የአፈር ማዳበሪያ እጥረት አሁንም ፈተና ሆኖ መቀጠሉን አርሶ አደሮች ተናገሩ

የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እጥረት በመላ አገሪቱ መከሰቱን ተከትሎ፤ አርሶ አደሮች የዘር ወቅት እያለፈባቸው በመሆኑ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የተለያዩ ክልል አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም የኦሮሚያ ክልል አርሶ አደሮች፤ በዘንድሮ የሰብል ልማት ወቅት ባጋጠማቸው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት የዘር ወቅት እያለፈብን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ፤ የማዳበሪያ አቅርቦቱ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ፣ ለሰብል ልማት ከሚያስፈልጋቸው የአፈር መዳበሪያ ፍጆታ ግማሽ ያህሉን እንኳን የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት በግብርና ሥራው ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አዲስ ማለዳ  ያነጋገራቸው የክልሉ አርሶ አደሮች ገልጸዋል፡፡

“የአፈር ማዳበሪያን በመጠቀም ምርታማነትን መጨመር ካልቻልን ወደ ገበያ የምናወጣውን የምግብ እህል ለራሳችን ብቻ ለመመገብ እንገደዳለን።” በማለትም ገልጸዋል፡፡ 

አርሶ አደሮቹ አክለውም፤ “ከዚህ በኋላ ማዳበሪያው እንደ ልብ ቢገኝም የዘር ጊዜ እያለፈ በመሄዱ ብዙም ዋጋ አይኖረውም።” ሲሉ ያላቸውን ስጋት አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል ያጋጠመውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ተከትሎ፤ በተለያዩ አካባቢዎች አርሶ አደሩ አደባባይ ወጥቶ ለመንግሥት ጥያቄ አቅርቧል። ይሁን እንጂ የማዳበሪያ አቅርቦቱ አልተስተካከለም፡፡

በተመሳሳይ በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን የሶዶ ወረዳ አርሶ አደሮች በአፈር ማዳበሪያ እጥረት ምክንያት አርብ ሰኔ 29/2015 ለኹለተኛ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን አዲስ ማለዳ ሰምታለች፡፡ 

በዚሁ ወረዳ የአፈር ማዳበሪያ ከባለሃብቶች እጅ መግባቱንና በገበያ አዳራሾች ጭምር እየተሸጠ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ አንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እስከ 11 ሺሕ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡

“በውድ ዋጋ ገበያ ላይ የሚቸረቸረው የአፈር ማዳበሪያ እንኳን በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩና በግብርና ቢሮዎች የተከማቸውም ማዳበሪያ ለገበሬው እየተሰጠ ባለመሆኑ ለኹለተኛ ጊዜ ሰልፍ እንድንወጣ አስገድዶናል።” ብለዋል አርሶ አደሮቹ፡፡

የአፈር ማደባሪያ እጥረቱ በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች መኖሩንም አዲስ ማለዳ ባደረገቸው ማጣራት ለማወቅ ችላለች፡፡ 

ባለሃብቶች እና ነጋዴዎች ከመንግሥት ሹማምንት ጋር ተመሳጥረው የሚሰሩት የማዳበሪያ ሽያጭ ለግል ሃብት ማከማቻ እየዋለ መሆኑን አርሶ አደሩ በምሬት እየተናገረ ይገኛል፡፡ 

በተለያዩ ክልሎች የአፈር ማዳበሪ እጥረትና መዘግየትን ተከትሎ አርሶ አደሩ ያነሳውን ጥያቄ ተከትሎ፤ መንግሥት በሰጠው ምላሽ ማዳበሪያ በሕገ ወጥ መንገድ እየተሸጠ መሆኑን አምኗል፡፡

መንግሥት ከአፈር ማዳበሪያው ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ሕገ ወጥ ሥራዎች በተግባሩ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ለይቶ በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበት አግባብ ይፈጠራል ሲል እንደነበርም ይታወሳል፡፡

በመንግሥት በኩል የአፈር ማዳበሪያ እየተጓጓዘ ነው የሚል ምላሽ ቢሰጥም፤ እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ የዘር ወቅት ካለፈ በኋላ ግብዓቱ ቢቀርብም ነገሩ “ጀብ ከሄደ ውሻ” ጮኸ አይነት ከመሆን ያለፈ ትርጉም አይኖረም ተብሏል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply