
የአፋር ፍርድ ቤት የአቶ ስንታየሁ ቸኮልን ጉዳይ የመዳኘት ሥልጣን እንደሌለው ቢገልፅም መዝገቡን እንዳይዘጋ ተከለከለ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በግፍ እስር ላይ የሚገኙት ፖለቲከኛው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ከአዲስ አበባ በግዞት ወደ አፋር፤ አዋሽ ሰባት ከተወሰዱ በኋላ ባለፈው የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ፍርድ ቤቱም በፌዴራል ፖሊስ የተከፈተባቸውን የሽብር የምርመራ ዶሴ የመዳኘት ሥልጣን እንደሌለው ገልጿል። ይሁን እንጂ መዝገቡን ዘግቶ ከማሰናበት ይልቅ የ11 ቀናት ቀጠሮ በመስጠት ለየካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። የካቲት 23 በየዓመቱ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ መሥሪያ ቤቶች ተዘግተው የአድዋ ድል በዓል የሚከበርበት ዕለት ሲሆን ችሎቱ ቢሰየም እንኳን ዶሴውን የመዳኘት ሥልጣኑ ሳይኖረው ዳኞች ምን እንደሚያዳምጡና ምን እንደሚበይኑ አይታወቅም። አቶ ስንታየሁ “ችሎቱ ጉዳየን የመዳኘት ሥልጣን ከሌለው ለምን መዝገቡን ዘግቶ አያሰናብተኝም? በሌለው ሥልጣን እኔን እስር ቤት አስቀምጦ ለምን ቀጠሮ ይሰጣል?” በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ችሎቱም “ሥልጣናችን ባይሆንም ቀጠሮ እንድንሰጥ ታዝዘናል። መዝገቡን መዝጋት አንችልም” ሲል መልሷል። የፖለቲካ እስረኛው በአዲስ አበባ ጎፋ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በጸሎት ላይ እያሉ ታግተው መታሰራቸው ይታወሳል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ የተደረገውን መንግሥታዊ የመፈንቅለ ሲኖዶስ ሙከራ ተከትሎ ከ2,500 በላይ ኦርቶዶክሳውያን ከአዲስ አበባ ወደ አዋሽ ሰባት የተጋዙ ሲሆን፤ ሁሉም ሲፈቱ አቶ ስንታየሁ ብቻ በእስር ቀጥለዋል። አቶ ስንታየሁ በየሦስት ወሩ የሚደረግ የህክምና ቀጠሮ እንዳላቸው ጠቅሰው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ቢጠይቁም ችሎቱ ከልክሏል። በአሁኑ ሰዓት አቶ ስንታየሁ ቸኮል አዋሽ 7 ሜሪድያን ሆቴል ጀርባ ይገኛሉ ተብሏል።
Source: Link to the Post