የአፍሪካን ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ ውድድር ነገ ይጀመራል

የአፍሪካን  ሮቦቲክስ  ቻምፒዮንሺፕ ውድድር  ነገ ይጀመራል

ኢትዮ – ሮቦ ሮቦቲክስ፤ በነገው ዕለት ሐሙስ፣ የ2024 የአፍሪካ ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ ውድድሩን በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል የሚጀምር ሲሆን፤ ቅዳሜ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ መርሃ ግብሩ  በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ ዓመታዊ የሮቦቲክስ ወድድር መሆኑን የኢትዮ-ሮቦ ሮቦቲክስ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰናይ መኮንን ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ  በነገው ዕለት የሚጀመረውን የሮቦቲክስ ውድድር አስመልክቶ ከማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ  አቶ ሰናይ መኮንን ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-

****

እስቲ ታዳጊዎች ባለፉት 6 ወራት በናንተ ማዕከል ውስጥ ስለወሰዱት የሮቦቲክስ ሥልጠና አብራሩልኝ?

ታዳጊዎች ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ፕሮግራሚንግ፣ ዲዛይኒንግ እና ኢንጅነሪንግ ላይ ያተኮረ የሮቦቲክስ ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ የመማር በተግባር መርህ ተከትለው በመስራት ለቬክስ ሮቦቲክስ ውድድር ተዘጋጅተዋል፡፡

ልጆቹ ከዚህ ሥልጠና በተጨባጭ የሚያተርፉት ምንድን ነው? በህይወታቸው ላይ ምን ይጨምራሉ?

በእነዚህ ጊዜያት የኢንጅነሪንግ ፣ የዲዛይኒንግ እና  የፕሮግራሚንግ ክህሎቶቻቸውን አሻሽለዋል፡፡ የራሳቸውን አዲስ ነገር የመፍጠርና የመሞከር እድል አግኝተዋል፡፡ በመጪው የዲጂታል ዘመን ውስጥ ብቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል፡፡
ባለፈው ጥር ወር በቻይና በተካሄደ ውድድር ላይ ተሳትፋችሁ ተመልሳችኋል? ውድድሩ ምን ይመስል ነበር? ውጤቱስ? በመሰል ዓለማቀፍ  ውድድሮች ላይ መሳተፍ ፋይዳው ምንድን ነው? የኛ ልጆች ከቻይናዎቹ አቻዎቻቸው ጋር ሲወዳደሩ ምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት?

ባለፈው ጊዜ በቻይና በነበረን ውድድር አበረታች ውጤት አይተናል፡፡ ለብዙ ተወዳዳሪዎች የመጀመሪያ ስለነበር፣ ከዚህ በኋላ በሌሎች አለም አቀፍ ውድድሮች ማለትም በአሜሪካና በካናዳ ለሚጠብቃቸው መሰል ውድድር የበለጠ ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ፡፡ ቻይናውያን እጅግ በጣም ከፍተኛ ዝግጅት አላቸው፤ በተለይም በትምህርት ካሪኩለማቸው ሮቦቲክስ እና ፕሮግራሚንግ የተካተተ ስለሆነ፤ ከኢትዮጵያውያን የበለጠ ውጤት በማምጣት በውድድሩ ላይ አንደኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

እስቲ  ነገ ሐሙስ በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል ስለሚጀመረው  የ2024 የአፍሪካ ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ በጥቂቱ ይንገሩኝ? በውድድሩ ሌሎች አፍሪካውያን ይሳተፋሉ እንዴ?

በነገው እለት በኢሊሌ ሆቴል የሚደረገው የአፍሪካን ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ የሚዘጋጅ አመታዊ የሮቦቲክስ ውድድር ሲሆን፤ በዚህ  ውድድር የተወሰኑ እዚሁ አዲስ አበባ የሚኖሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች ይሳተፋሉ፡፡ ውድድሩን ይበልጥ ሌሎች አፍሪካዊ ተማሪዎች የሚሳተፉበት ለማድረግ ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡

ኢትዮ – ሮብ ሮቦቲክስ ከተከፈተ ምን ያህል ጊዜ ሆነው? እስካሁን ምን ያህል ተማሪዎች አስመርቃችኋል?

አፍሪካን ሮቦቲክስ ቻምፒዮንሺፕ ያልነው፣ ሮቦቲክስ ስንጀምር በአፍሪካ የመጀመሪያዎች እኛ በመሆናችን ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው ደግሞ በ2011 ዓ.ም  እኛ ከብዙ አለም አቀፍ የሮቦቲክስ ኩባንያዎች  ጋር  ስንፈራረም፣ ሌሎች  የአፍሪካ አገራት  ቀድመው አልተፈራረሙም ነበር፡፡ ሁለተኛ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ አገር ከመሆንዋ አንጻር ለዚህ ውድድር ከሌላ አገር የበለጠ ተመራጭ ያደርጋታል፡፡

እናንተ ዘንድ  በሮቦቲክስ ሰልጥነው ትልቅ ቦታ የደረሱ ኢትዮጵያውያን  አሉ?

በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስልጠና  ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ  ወደ አሜሪካና ካናዳ ሄደው ስኮላርሺፕ ያገኙና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት እየተማሩ ያሉ፣ ከ100 በላይ ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት አገራቸውን አስተዋውቀዋል፡፡ ለወደፊት ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ስራ አለም ሲገቡ የምናያቸው ይሆናል፡፡ አሁን በስራ ላይ ካሉት ውስጥ  ሳሙኤል አርአያ በኦንላይን ስራ የሚጠቀስ ጎበዝ ልጅ ነው፡፡

ከሮቦቲክስ ሥልጠና ሌላ ቋንቋም ታስተምራላችሁ አይደል?

የቋንቋና የሰልፍ ዲስፕሊን ኮርስም ለህጻናት እንሰጣለን፡፡ በቋንቋ ስልጠናችን ለተማሪዎች ለየት ባለ ሪድ ኤንድ ቴል ፕሮግራማችን፣ ልዩ ልዩ በልምምድ ላይ ያተኮረ  ስልጠና እንሰጣለን፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply