የአፍሪካ ሕብረት የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ወደ ሌላ ሀገር ሊያዘዋውር ነው በሚል የተሰራጨው መረጃ “የተሳሳተ” ነው ሲል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀ…

የአፍሪካ ሕብረት የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ወደ ሌላ ሀገር ሊያዘዋውር ነው በሚል የተሰራጨው መረጃ “የተሳሳተ” ነው ሲል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢዩ ተድላ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአፍሪካ ሕብረት በግቢው ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ በንክ ሒሳቡ ላይ በሀሰተኛ ሰነድ ገንዘብ ለማዘዋወር የተደረገበትን ሙከራ ተከትሎ “ከሕብረቱ ጋር ባደረግነው ቀጥተኛ ውይይት ይህ አይነት እሳቤ በተቋሙ ውስጥ እንደሌለ የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕብረቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት “በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለው የድርጅቱ ሒሳብ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተጠበቀ እንደሆነ” መናገራቸውንም ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

የተፈጠረው ክስተት በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያስከተለው ተጽዕኖ ስለመኖር አለመኖሩ የተጠየቁት ቃል ዐቀባዩ “ሙከራ ነው። ጉዳዩ በሕግ ያለ ነው። ዝርዝር ልንናገር አንችልም።

የተሞከረው ጥቃት ግን ከሽፏል። ጉዳዩ ወደ ሌላ ደረጃ ሳያልፍ ወይም ጉዳት ሳያስከትል ለመቆጣጠር ተችሏል” በማለት መልሰዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ የሆኑት ቀሲስ በላይ መኮንን ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ሕብረት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በአካል በመገኘት “ከአፍሪካ ሕብረት የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ” በተባሉ ሐሰተኛ ሰነዶች፤ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ከሕብረቱ የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ ለማዘዋወር ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

በጉዳዩ ላይ ከቀናት በፊት ማብራሪያ የጠየቃት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን “ሊቀ ዐዕላፍ በላይ መኮንን በሕግ ጥላ ሥር የዋሉበት ጉዳይ ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር የሚያገናኘው ምንም ጉዳይ እንደሌለ፤ በግል ሕይወታቸው ውስጥ የገጠማቸው ነገር እንደሆነ ነው የተረዳነው” የሚል ምላሽ ተሰጥቶት ነበር።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply