የኢሚግሬሽን ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ደሳለኝ ተሬሳን ጨምሮ የተቋሙ 10 ባለሙያዎችና ደላላ ናቸው የተባሉ 5 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

ሐሙስ ሐምሌ 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በጥቅም በመመሳጠር ያለአግባብ ለግለሰቦች ፖስፖርት እንዲሰራ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ የኢሚግሬሽን ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ተሬሳን ጨምሮ የተቋሙ 10 ባለሙያዎችና ደላላ ናቸው የተባሉ 5 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

በተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ማህተሞች፣ የተለያዩ ሰነዶች፣ በርካታ የተዘጋጁ ፖስፖርቶችና ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ያላቸው የተለያዩ የባንክ ደብተሮችና ጥሬ ብር እና ሽጉጥ ማግኘቱን ፖሊስ ለፍርድ ቤት ዘርዝሯል።

ከትናንት በስትያ በቁጥጥር ሥር ውለው ትናንት ከሰዓት ላይ ፍርድ ቤት ከቀረቡ ተጠርጣሪዎች መካከል የመጀመሪያ ደረጃ የፍርድ ቤት ማህተሞች በመኖሪያ ቤቱ የተገኘበት የተቋሙ ሠራተኛ አብይ በላይ እና በመኖሪያ ቤቱ በተደረገ ብርበራ የተገኘ 270 የአሜሪካ ዶላር በአየር መንገድ በደህንነት ሥራ የተሰማራችው የባለቤቱ መሆኑን የገለጸው በግል ሥራ የሚተዳደረው እዮብ አማረ የተባለ ግለሰብ ይገኙበታል።

ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ያዋለው የፌደራል ፖሊስ መርማሪ የተጠረጠሩበትን መነሻ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በጥቅም በመመሳጠር ያለቀጠሮ ገንዘብ በመቀበል ለግለሰቦች ፖስፖርቶችን በማዘጋጀት ሲሰጡ ነበር ብሎ መጠርጠሩን ፖሊስ ለችሎቱ አብራርቷል።

በተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ማህተሞች፣ የተለያዩ ሰነዶች፣ በርካታ የተዘጋጁ ፖስፖርቶችና ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ያላቸው የተለያዩ የባንክ ደብተሮችና ጥሬ ብር ማግኘቱንም ዘርዝሯል።

ለተጀመረው ምርመራ ተጨማሪ ማስረጃ ተመሰብሰብና መዝገቡን አደራጅቾ ለማቅረብ፣ ግብረአበር ለመያዝ፣ የተጠርጣሪዎችን እና የምስክር ቃል ለመቀበል የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የኢሚግሬሽን ዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ደሳለኝ ተሬሳ በበኩላቸው፤ መረጃን ለህዝብ እና ለሚዲያ የማድረስ ሥራ ውጪ ከወንጀሉ ጋር የሚያገናኛቸው ጉዳይ እንደሌለ ገልጸዋል።

በመኖሪያ ቤታቸው የተገኘው ሽጉጥ ከ2 ዓመት በፊት በፍትህ ሚኒስቴር በቃል አቀባይነት ሲሰሩ የተሰጣቸውና ፍቃድ ያለው መሳሪያ መሆኑን ለችሎቱ በማስረዳት የዋስ መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

ሌላኛው ተጠርጣሪ የመጀመሪያ ደረጃ የፍርድ ቤት ማህተሞች በመኖሪያ ቤቱ እንደተገኘት በችሎት ያመነው የተቋሙ ሠራተኛ አብይ በላይ በበኩሉ፤ የፍርድ ቤት ማህተሞችን አዱኛ የሚባል የሚያውቀው ግለሰብ እንደሰጠውና 6 ወር በመኖሪያ ቤቱ እንዳስቀመጠው ገልጿል።

የጆሮ ህመምተኛ መሆኑን ተከትሎ የህክምና ቀጠሮ እንዳለው በመግለጽ ዋስትና እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

በመኖሪያ ቤቱ በተደረገ ብርበራ የተገኘው 270 የአሜሪካ ዶላር በአየር መንገድ በደህንነት ሥራ የተሰማራችው የባለቤቱ ብር መሆኑን የገለጸው እዮብ አማረ የተባለው ተጠርጣሪ ሲሆን፤ በስቴሺነሪ ንግድ ሥራ እና የኦላይን ሥራ ላይ መሰማራቱን ጠቅሶ የተገኘው 270 ዶላር ባለቤቱ ከአየር መንገድ የተሰጣትና በቤት ያስቀመጠችው ብር እንደሆነ አብራርቷል።

አብርሐም እንዳለ የተባለ ሌላኛው ተጠርጣሪ፤ በ4 ኪሎ ቅርጫፍ በውጭ አገር ደንበኞች ዘርፍ ላይ እንደሚሰራ ገልጾ፤ በቤቴ የተገኘው 52 ሺህ ብር ዕቃ መግዣ የተቀመጠ ነው ሲል አብራርቷል።

ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽም ዋስትና እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

ሌላው ተሻለ ሌሊሳ የተባለ ተጠርጣሪ በበኩሉ፤ “በዋናው ቢሮ የኢሚግሬሽን የጉዞ የሰነዶች ምዝገባና አሰጣጥ ቡድን መሪ ሆኜ ከመስራቴ ውጪ ከጉዳዩ ጋር የሚያገናኝ ነገር የለም” ሲል ገልጿል።

ለማስተርስ ፈተና እንደደረሰበትም ገልጾ ዋስትና እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

ቀሪዎቹ የተቋሙ ሠራተኞች በአራት ኪሎ ቅርጫፍ በውጭ ዜጎች አስተዳደርና የሰነድ ማጣራት ዘርፍ መሰማራታቸውን ገልጸው፤ ከጉዳዩ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ በማብራራት ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

የሻይና ቡና በማዞር ሥራ እንደምትተዳደር የገለጸችው ሻለወርቅ ተድላ የተባለች በድለላ ሥራ የተጠርጣረች ግለሰብን በተመለከተ፤ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት እንደሌላት ገልጻ ህጻን ልጅ ቤት ካለጠባቂ አስቀምጣ በቁጥጥር ሥር መዋሏን በመግለጽ ዋስትና እንዲፈቀድላት ጠይቃለች።

ሌላኛው ዳንኤል ተክሌ የተባለ ተጠርጣሪ በበኩሉ፤ የራይድ ሹፌር መሆኑን በመግለጽ በመኖሪያ ቤቱ በብርበራ የተገኘ 90 ሺህ ብር ባለቤቱ ላይ የመኪና አደጋ ደርሶ ለህክምና የሚከፈል መሆኑን ገልጿል።

ቀዳማዊ ሞገስ የተባለው ሌላኛው ተጠርጣሪ ደግሞ፤ በኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ የማማከር ሥራና በገቢዎች ሪፖርት በመስራት እንዲሁም ዱባይ ኳታር እና ጉዳይ በማስፈጸምና ፖስፖርት ሥራ ላይ በግሉ የኦላይን አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጿል።

ተጠርጣሪው በተጨማሪም በመኖሪያ ቤቱ ፖሊስ ያገኘው ሽጉጥ የአጎቱ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ የተገኘ ሌላ ፖስፖርት የአክስቴ ነው ሲል አብራርቷል። “ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ስለሌለኝ ዋስትና መብቴ ይጠበቅ” ሲልም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ የሚያደርሱት ጉዳት ምን እንደሆነ ለማረጋገጥ ጥያቄውን ለፖሊስ ያቀረበ ሲሆን፤ ፖሊስ ቢወጡ የተጀመረው ምርመራ ሊያደናቅፉ እንደሚችሉ በመግለጽ ምስክርና ግብረአበር ሊያሸሹ ይችላሉ ሲል ዋስትናውን በመቃወም ምላሽ ሰጥቷል።

ጉዳዩን የመረመረው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ምርመራው ሰፊና ውስብስ ከመሆኑ አንጻር የተጀመረው ምርመራ ሊያደናቅፍ ይችላል በማለት የተጠርጣሪዎችን ዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ለፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ማከናወኛ 14 ቀን መፍቀዱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።

Source: Link to the Post

Leave a Reply