የኢሬቻ በዓል የዋዜማ ስነ ስርዓት በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል የዋዜማ ስነ ስርዓት በርካታ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ተሳታፊዎች በተገኙበት በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው፡፡

በአዲስ አበባ እየተካሄደው በሚገኘው በዚህ የኢሬቻ የዋዜማ ስነ ስርዓት ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ፣ አባ ገዳዎች እና ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል የመጡ ታሳታፊዎች እየታደሙ ይገኛል፡፡

በዚህ ዋዜማ በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ አዲስ አበባ ከተማ የኢሬቻን በዓል ስታከብር የሁሉም ኢትዮጵያዊያን በመሆኗ እና የሁሉም እንድትሆን በማሰብ ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው የኦሮሞ ህዝብ ይህን በዓል በነፃነት በዚህ ስፍራ እንዲያከብር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጰያዊያን መስዋዕትነት ከፍለዋል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም የኢሬቻ በዓል በኢትዮጵያ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ በደማቅ ስነ ስርዓት እንዲከበር አስተዋፅኦ ለማበረከቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የኢሬቻ በዓል የሰላም ፣ የነፃነት እና የእኩልነት ነው ያሉ ሲሆን በሁሉም ቦታዎች በታላቅ ድምቀት የምናከብረው ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ኢትዮጵያ እኛ ትመስላለች ፤ እኛን እንድትመስል ማድረግም የእኛ ሃላፊነት ነው ፤ እኛን እንድትመስል ማድረግም የሚቻለውም እርስ በእርስ ተደጋግፈን ማንነታችንን በልማት ፣ ፓለቲካ ፣ በቴክኖሎጂ በሁሉም መድረክ እንዲፀባረቅ ጠንክሮ በመስራት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ይህንን ተግባራዊ እና ስኬታማ ለማድረግ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በመስራት ነው ሲሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል፡፡

ለውጡ እንደ ወጋገን፣ ፍትህ ፣ እኩልነት ችግሮችን እየፈታ ይሄዳል ያሉ ሲሆን የህዝቡን ነፃነት ወደ ኋላ የሚመልስ አካል የለም ብለዋል፡፡

የዋዜማ ስነ ስርዓቱ በአባ ገዳዎች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን የተለያዩ ስነ ስርዓቶች በዚህ በዓል ላይ እየቀረቡ ይገኛል፡፡

በዚህ የኢሬቻ የዋዜ ስነ ስርዓት ላይ በዋነኝነት የተለያዩ የባህል ስነ ስርዓቶች እንደሚቀርቡ ነው የሚጠበቀው፡፡

Leave a Reply