የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር የሚያዘጋጀዉ 60ኛ ዓመታዊ ጉባዔ እና ዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽን በመካሄድ ላይ ነዉ፡፡ማህበሩ ወቅታዊ የሆኑ ከጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ እና የማህበረሰብ ፍላጎት የሆ…

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር የሚያዘጋጀዉ 60ኛ ዓመታዊ ጉባዔ እና ዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽን በመካሄድ ላይ ነዉ፡፡

ማህበሩ ወቅታዊ የሆኑ ከጤና ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ እና የማህበረሰብ ፍላጎት የሆኑ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸዉ የሚለዉ ላይ ትኩረት አድርጎ በየዓመቱ የሚዘጋጀዉ ጉባዔ በዛሬዉ ዕለት በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተግባር ይግዛዉ እንዳሉት፤የዚህኛዉ ዓመት የጉባዔዉ መወያያ ርዕስ ታካሚ እና ማህበረሰብ ተኮር የሆነ የጤና አገልግሎት ማሳካት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነዉ ብለዋል፡፡

ሰዎች ወደ ህክምና ተቋማት ሄደዉ የሚያገኙት አገልግሎት ምን ይመስላል የሚለዉን ፤ ከዋጋ አንጻር በተለይ ደግሞ በግል ህክምና ተቋማት ላይ የሚታዩ ሁኔታዎች እንዲሁም የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ተገልጋይ ተኮር የህክምና አገልግሎትን እንዴት መስጠት እንችላለን የሚለዉን እንዲሁም በምን ዓይነት መንገድስ ማሳካት እንችላለን የሚለዉ ሀሳብ በስፋት ዉይይት ይደረግበታል ብለዉናል፡፡

ታካሚ ተኮር እና የማህበረሰቡን ፍላጎት የሚያሟላ የጤና ስርዓት እንዲኖር ደግሞ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከህክምና ማህበር ፣ ከግሉ ጤና ሴክተር፣ ከባለሙያዉ እንዲሁም ከማህበረሰቡ ምን ይጠበቃል የሚለዉን ጉዳይ የምንነጋገርበት ይሆናል ነዉ ያሉት፡፡

በጉባዔዉ ላይ ከዉይይቱ ባሻገር ለረጅም ጊዜ ላገለገሉ የህክምና ባለሙያዎች እና ወጣት ባለሙያዎች ዕዉቅና ተሰጥቷል፡፡

የህክምና ማህበሩ ባሉት 14 ቅርንጫፎች ላይ ያሉ ለማህበረሰቡ መልካም ላደረጉ የህክምና ባለሙያዎችም ዕዉቅና ሰጥቷል፡፡

ጉባዔዉ እና ዓለም ዓቀፍ የጤና ኤግዚቢሽኑ ዛሬ እና ነገ ቀጥሎ የሚካሄድ ይሆናል፡፡

በእስከዳር ግርማ

የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply