የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር አባል የነበረው አርበኛ ሀብታሙ ባዬ አሁኑ ላይ የእነ አንጋፋው ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ፣የእነ አርበኛ ሰላማዊት ጌጡና የሌሎች ጓዶቹ፣ የመላው አማራ ብሎም የኢት…

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር አባል የነበረው አርበኛ ሀብታሙ ባዬ አሁኑ ላይ የእነ አንጋፋው ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ፣የእነ አርበኛ ሰላማዊት ጌጡና የሌሎች ጓዶቹ፣ የመላው አማራ ብሎም የኢትዮጵያን የጋራ ጠላት የሆነውን ወያኔን በግንባር ተሰልፎ እያሳደደ መሆኑን አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አማሚ ታህሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ አርበኛ ሀብታሙ ባዬ ይባላል። የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ኢህአግ አባል በመሆን በኤርትራ በርሃ ከባለቤቱ አርበኛ ሰላማዊት ጌጡና የትግል ጓዶቹ ጋር በመሆን ተሰልፎ በሽብር ተግባር የተሰማራውን ወያኔን ታግሏል። በኢትዮጵያ የተጀመረው ህዝባዊ ተጋድሎና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉት የአርበኞች እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ መምጣቱን ተከትሎ ወያኔ መራሹ መንግስት በግፍ ያሰራቸውን አብዛኞችን የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን ይፈታ ዘንድ የግድ ሆኗል። ከህዝባዊ የለየለት የለውጥ እንቅስቃሴ ባሻገር በድርጅቱ ውስጥ የነበሩ ለውጥ እንፈልጋለን የሚሉ የአንዳንድ አመራሮች ድጋፍ ተጨምሮበት በውጭ የነበሩ አርበኞች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ሲደረግ ከመጡት መካከል አንዱ ነው_አርበኛ ሀብታሙ ባዬ። አርበኛ ሀብታሙ በኤርትራ በርሃ ስለአማራ ብሎም ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ስትል ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለችውን ታጋይ ባለቤቱን ሰላማዊት ጌጡን ባለፈው ዓመት በሞት መነጠቁ ይታወሳል። አርበኛ ሀብታሙ አሁን ላይም በአማራ ልዩ ሀይል ሰልጥኖ የአሰልጣኛቸው፣የደጋፊያቸው፣በችግር ጊዜ ደራሻቸው፣የአርበኞች ባለውለታ የሆኑትን የጋዜጠኛ እና አርበኛ ደምስ በለጠን፣የእነ አርበኛ ሰላማዊት ጌጡንና የጓዶቹን ብሎም የአማራንና የመላው ኢትዮጵያን ጠላት ፊት ለፊት መፋለሙን ተናግሯል። መንግስት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ላለፉት ሁለት ወራት በመቀሌ እና በተምቤን በግዳጅ ተሰልፈን ከሃዲውን በተደበቀበት ምሽግ እያፈላለግን በመደምሰስ ላይ እንገኛለን ብሏል_ከምሽግ ወጥቶ ያነጋገረን አርበኛ ሀብታሙ ባዬ። መንግስት ልምድ አላቸው፣ ድሮም የመከላከያ አባል ነበሩ በሚል የተወሰኑ አርበኞችን ለይቶ የመከላከያ ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ያስታወቀው አርበኛ ሀብታሙ የኢትዮጵያን ጠላት ወያኔን አይቀጡ ቅጣት ከቀጡትና እየቀጡ ከሚገኙት መካከል አንዱ መሆኑን ገልጧል። አርበኛ ሀብታሙ የጋዜጠኛ ደምስ በለጠን ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያን በተመለከተ በግዳጅ ቀጠና እያለ በስልክ አነጋግረነዋል። ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ቤተሰባቸውን በትነው ለታጋዮች ከባድ ውለታ የዋሉ ስለመሆናቸው፣ ከአመራሩ ጋር አመራር፣ከአባሉ ጋር አባል፣ከተዋጊው ጋር ተዋጊ ሆነው ዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦ ያበረከቱ፣ አንድ ቤት ያለምሰሶ እንደማይቆም ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር የኢህአግ መሰረት አንጋፋ ታጋይ ነበሩ ሲል ገልጧቸዋል። ታህሳስ 13 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚናፍቋቸው፣ ለበርካታ ዓመታት ተለያይተው ቆይተው ካገኟቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር በነበሩበት ወቅት ከምግብ ምረዛ ጋር በተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ በተነገረለት ሁኔታ በግፍ የተገደሉት አርበኛ እና ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ በሁሉም ዘርፍ ባደረጉት ተጋድሎ የአርበኞች፣የአማራና የለውጥ ፈላጊ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ባለውለታ መሆናቸው ይታወቃል። የአማራ ሚዲያ ማዕከልና የአማራ ድምፅ ራዲዮ የአርበኛና ጋዜጠኛ ደምስ በለጠን ሁለተኛ ዓመት ህልፈትን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚዘክር ይሆናል። በግዳጅ ላይ ካለው ከአርበኛ ሀብታሙ ባዬ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በአማራ ሚዲያ ማዕከል የዩቱብ አድራሻ ይጠብቁ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply