የኢትዮጵያ መንግስት፤ አሜሪካ ለህወሓት የመወገን “ግልጽ ጦርነት” በኢትዮጵያ ላይ ከፍታለች አለ

የኢትዮጵያ መንግስት፤ አሜሪካ ለህወሓት ቡድን የመወገን “ግልጽ ጦርነት” በኢትዮጵያ ላይ ከፍታለች አለ። የአሜሪካ መንግስትም ሆነ በአዲስ አበባ የሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ኢትዮጵያን በሚመለከት ከሚያወጧቸው “አሸባሪ፣ አሳፋሪ እና ኃላፊነት የጎደላቸው” መግለጫዎች እንዲቆጠቡም አስጠንቅቋል።  

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ዛሬ ሐሙስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የአሜሪካ ኤምባሲ እና አንዳንድ የአሜሪካ መንግስት ተወካዮች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያሉት ጫና “እጅግ አሳፋሪ በሆነ መንገድ” እና “በማይገባ መስመር ቀጥሏል” ብለዋል። ሚኒስትር ዲኤታው ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል በአሜሪካ ኤምባሲ የወጣውን ማስጠንቀቂያ ነው። 

ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ጀምሮ አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና በአሜሪካ መንግስት ተቋማት የተሰራጨው መልዕክት፤ በኢትዮጵያ አሸባሪዎች ያለ ምንም ቅደመ ማስጠንቀቂያ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ ስለሚችሉ የአሜሪካ ዜጎች ራሳቸውን ከአደጋ እንዲጠብቁ የሚያሳስብ ነው። ኤምባሲው በዚሁ መልዕክቱ አሸባሪዎች በኢትዮጵያ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ተቋማትን፣ የቱሪስት ቦታዎችን፣ የትራንስፖርት ማዕከላትን፣ የመገበያያ ስፍራዎችን፣ በምዕራባዊያን ባለቤትነት የተያዙ የንግድ ድርጅቶችን፣ ምግብ ቤቶችን፣ ሪዞርቶችን፣ የመንግሥት ተቋማትን እንዲሁም ሌሎች ህዝብ የሚበዛባቸውን ቦታዎችን ኢላማቸው ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።

ይህንን የአሜሪካ ኤምባሲን ማስጠንቀቂያ “ማስፈራሪያ እና ሽብር የሚፈጥር መግለጫ” ሲሉ ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸውታል። መግለጫው  “ኢትዮጵያውያንን የማስፈራራት እና የዓለም ማህብረሰብ ኢትዮጵያ ሰላም የላትም እንዲል” ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ተናግረዋል። የአሜሪካ ማስጠንቀቂያ “ ‘አዲስ አበባ ለሽብር ጥቃት የተጋለጠች ነች’ በማለት ባለሃብቶች፣ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ለማድረግ እና የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማበላሸት ያለመ መግለጫ መሆኑን እንገልጻለን” ብለዋል።   

“እንደዚህ አይነት ተግባራት የዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ህጎች እና ልማዶችን የሚጥሱ፤ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ታሪካዊ፣ ሰላማዊ ግንኙነትን የሚንዱ እና የሚያበላሹ መሆኑን እየገለጽን፤ በዚህ አጋጣሚ የአሜሪካ መንግስትም ሆነ አዲስ አበባ ውስጥ ተቀማጭነቱን ያደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ ከእንደዚህ አይነቱ አሸባሪ፣ አሳፋሪ እና ኃላፊነት የጎደለው መግለጫዎች ራሱን እንዲቆጥብ እናስጠንቅቃለን” ሲሉ አቶ ከበደ የኢትዮጵያን መንግስት አቋም አስታውቀዋል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

The post የኢትዮጵያ መንግስት፤ አሜሪካ ለህወሓት የመወገን “ግልጽ ጦርነት” በኢትዮጵያ ላይ ከፍታለች አለ appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply