የኢትዮጵያ መንግስት በሰብአዊ መብት ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ማቆም አለበት ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጸ፡፡የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሲቪክ ምህዳሩ እና ገለልተኛ የሀገር ውስጥ የሰብአዊ…

የኢትዮጵያ መንግስት በሰብአዊ መብት ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ማቆም አለበት ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሲቪክ ምህዳሩ እና ገለልተኛ የሀገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ እየወሰዱ ያለዉን አካላዊና ዲጂታል ክትትል፣ የቃላት ትንኮሳ፣ ማስፈራራት እና ዛቻን ጨምሮ እያባባሱ ያሉትን እርምጃዎች በአስቸኳይ ማቆም አለባቸው ሲሉ አምስት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዛሬ አስታዉቀዋል።

እነዚህ ድርጊቶች አስደንጋጭ ምልክትን የሚልኩ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም በሀገሪቱ ውስጥ የሰብአዊ መብቶችን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ተግባራቸውን እንዳይፈጽሙ ያግዳቸዋል ብለዋል፡፡

ከቅርብ ወራት ወዲህ የኢትዮጵያ የደህንነት እና የስለላ ሃይሎች በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ነፃ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ጨምሮ በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ ታዋቂ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ የሚያደርሱትን ማስፈራራት፣ ወከባ እና ዛቻ ጨምረዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ከጥር 2024 ጀምሮ የመንግስት የደህንነት ሃይሎች የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሰራተኞችን በስራ ቦታቸዉ እና በመኖሪያ ቤታቸዉ ጭምር በመከታተል የሰብዓዊ መብት ክትትላቸዉን እንዲያቆሙ እና ሪፖርት ማድረጋቸዉንም እንዲያቆሙ ማስገደዳቸዉን ነዉ የገለጹት፡፡ ማስፈራራቱ እና ዛቻዉ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ደግሞ በእጅጉ መጨመሩን አምነስቲ አስታዉቋል፡፡

በግንቦት 23 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ቢሮን የደህንነት አባላት መረጃ ፍለጋ በሚል መበርበራቸዉን እና በሂደቱም ሁለት የቢሮዉ ሰራተኞች ላይ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ማድረሳቸዉን እንደምሳሌ ያነሳዉ አምነስቲ፤ ኢሰመጉ በዛዉ ወር ላይ እየደረሰበት ያለዉ ማስፈራሪያ እና ዛቻ አሁንም ተባብሶ መቀጠሉን አስታዉቆ ነበር፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ካለፈዉ ዓመት ነሃሴ ጀምሮ አዲስ ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ ሲቪል ድርጅቶችን መመዝገብ ማቆሙ እንዳሳሰባቸዉ መግለጻቸዉን አምነስቲ አስታዉቋል፡፡

የተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎች ያቋቋሙት የኢትዮጵያ የፕረስ ነጻነት ተሟጋቾች ባወጣዉ አዲስ ሪፖርት ላይ ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ ወደ 2መቶ የሚጠጉ ጋዜጠኞች በመንግስት መታሰራቸዉን ይፋ አድርጓል፡፡

ኮሚቴዉ እስከ 2023 ድረስ ደግሞ 8 ጋዜጠኞች በወህኒ ቤት እንደሚገኙ ገልጾ፤ አራቱ ጋዜጠኞች በሽብር ወንጀል የተከሰሱ መሆናቸዉን በማንሳት ጥፋተኛ ሆነዉ ከተገኙ የሞት ቅጣት ሊጠብቃቸዉ እንደሚችል መግለጹን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል፡፡

እስከዳር ግርማ

ሰኔ 11ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply