የኢትዮጵያ መንግስት ብርን የማራከስ ሂደትን መግታት አለበት- ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ

የኑሮ ውድነት ኢትዮጵያውያንን ማሳሰብ ከጀመረ ሰነባብቷል። የዕለት ተዕለት ፍጆታዎች ዋጋ በየጊዜው መናር መካከለኛ እና ከዚያ በታች ኑሮ ላላቸው ዜጎች ራስ ምታት ነው። አዲስ ማለዳ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመታዘብ፣ ነዋሪዎች፣ የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎች፣ የምግብና መጠጥ አቅራቢዎች እንዲሁም የምጣኔ ሐብት ምሁር አነጋግራለች።

አንዲት እናት የኑሮ ውድነትን የዓመታት ጫና ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ “ከዓመታት በፊት ለቤቴ አስፈጭ የነበረው ጤፍ 50 ኪሎ ነበር። ዋጋው ሲጨምር ግን 25 ኪሎ እና ከዛም ያነሰ ማስፈጨት ጀምርኩ። አሁን ጭራሹኑ ትቻለው እንጀራ እየገዛን ነው የምንኖረው” ብለዋል። 

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻት የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴ ደግሞ “በፊት ከመርካቶ እቃ አምጥተን ሱቆ ሞልቶ እቃ የት እንደርድር ነበር የምንለው፤ አሁን በርካታ ገንዘብ ይዘን ጥቂት እቃ ብቻ ነው ማምጣት የምንችለው። መፍትሔው ምን እንደሆነ አላውቅም” ስትል ስጋቷን ገልጻለች። ይህችው ነጋዴ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ዘይት ባለ5 ሊትር ከ300 ብር ወደ 360 ብር ሲጨምር እጅግ ተገርማ እንደነበር ገልጻ አሁን 800 ብር መግባቱ “ያስደነግጠኛል” በማለት ትገልጻለች።

የምጣኔ ሐብት ምሁሩ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ አሁን ያለው የዋጋ ንረት በክፍለ አገርም ሆነ በከተማ ነዋሪ ላይ ጫና ይፈጥራል ብለው በከተማ ነዋሪ ላይ ተጽዕኖው እንደሚበረታ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በከተማው ውስጥ ያለው ነዋሪ በግልም ይሁን በመንግስት ተቀጥሮ የሚሰራው “70 በመቶ” የሚሆነው ነዋሪ ከ5 ሺህ ብር በታች ደሞዝ ተከፋይ እንደሆነም ባለሞያው ጠቁመዋል።

ገበሬው ምርት ስለሚያመርት ያን ያህል የማይቸገር ቢሆንም “ዝናብ ከሌለ አንድ ድርቅ ቢከሰት በቀጥታ ወደ ረሃብ ነው የሚገባው፤ አንድ ዝናብ እንኳን መሻገር አይችልም” ሲሉ የዋጋ ንረትን መዘዝ ያስረዳሉ። ታዲያ ባለፉት ኹለትና ሶስት ዓመታት ደመወዝ ለተጨመረለትም ላልተጨመረለትም የዋጋ ንረቱ 35 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ያሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ፤ ህዝቡ እንዴት አድርጎ እየኖረ እንደሆነ የሚያስገርማቸው ጉዳይ መሆኑ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻት በምግብ ቤት ሥራ ላይ የተሰማራች ሴትም ለምግብ ግብዓቶች የምትጠቀማቸው ምርቶች ዋጋ ከመጨመራቸው በላይ፤ ደንበኞቿ የተጠቀሙትን ለመክፈል ሲቸገሩ እንዳስተዋለች ነግራናለች። 

አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ የሚሰማው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች መረጃ እውነት ነው? ስትል ላቀረበችው ጥያቄ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ “እዚ አገር ላይ ትልቁ በሽታ ቁጥርን የማጋነን ችግር አለ። በዘመነ ኢሕአዴግ በ11 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል ሲል ያኔ እኔና ጓደኛዬ በሰራነው ምርምር 6 በመቶ ዕድገት ብቻ ነበር የተመዘገበው” ሲሉ አስታውሰው፤ የብልጽግና መንግስትም “ዕድገት ተመዘገበ የሚለው 7 ነጥብ 9 ቢሆንምም እኔ በሠራኹት ግምት ግን 4 ነጥብ 5 በመቶ ነው የተመዘገበው” በማለት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሆኖም ግን ይላሉ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ “ኢኮኖሚው ቢያድግም እንኳን የእያንዳንዱ ሠው ገቢ ኢኮኖሚው ባደገበት መጠን ካልጨመረ ለሕብረተሰቡ ምንም ጥቅም የለውም” ብለው ምጣኔ ሐብቱ አድጎ የሕብረተሰቡ ገቢ አብሮ ቢያድግ እንኳን “የዋጋ ንረት ካለ አሁንም የኢኮኖሚው ማደግ ዋጋ አይኖረውም” ሲሉ አሳስበዋል። 

በተጨማሪም “ዕድገቱ የተዛባ የገቢ ስርጭት ስለሚፈጥር”፤ ኢትዮጵያ ላይ ደግሞ የዋጋ ንረትም፣ የተዛባ ስርጭትም ስላለ ሰፊው ሕዝብ ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል ባለሞያው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። 

የመንግስት መስሪያ ቤት ሠራተኛ እና የሦስት ልጆች አባት የሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ደግሞ በእያንዳንዱ ነገር ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ያማርራል ብሏል። “የሚከፈለኝ ደመወዝ እና የማወጣው ወጪ ፈጽሞ አይገናኝም” የሚለው ቤተሰብ አስተዳዳሪው፤ ሁለት ልጆቹን ከግል ትምህርት ቤት ወደ መንግስት ትምህርት ቤት ለማዘዋወር መገደዱን ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። 

በኢትዮጵያ በተለይም ቋሚ ወርሃዊ ደመወዝ ያላቸው እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች በየጊዜው የሚጨምረው የዋጋ ንረትን መቋቋም እየከበዳቸው እንደሆነ በየጊዜው ይነሳል። የዋጋ ንረቱም በመንግስት ሠራተኛ አልያም በግል ተቀጥረው ለሚሰሩ ዜጎች የቤት ኪራይ፣ የምግብ ወጪ እንዲሁም የመጓጓዣ ወጪ አውጥቶ መኖር እጅግ ፈታኝ እንደሆነ በርካቶች ይገልጻሉ።

የምጣኔ ሐብት ምሁሩ ፕሮፌሰር ዓለማዩሁ ገዳ “ግሽበት ማለት አቅም አጣ ደከመ ማለት ነው”፤ ዋጋ ግሽበት ማለት ደግሞ ዋጋ ደከመ ሲሆን ዋጋ ሲበረታ ብር ነው የገሸበው ብለዋል። ስለዚህ “የዋጋ ንረት” አልያም “የገንዘብ ግሽበት” የሚለው አገላለጽ የተሻለ ነው ይላሉ።

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ በእርሻ በኩል ያለው ምርታማነት ከህዝቡ ቁጥር ጋር የማይጣጣም መሆኑ ለዋጋ ንረት እንደ ዋነኛ ምክንያት ያነሱት ሲሆን ከንጉሱ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የህዝብ ቁጥር አራት እጥፍ መጨመሩን ገልጸዋል። 

ሆኖም ግን ባለፉት 50 ዓመታት የምርታማነት መጠን ያደገው በሦስት በመቶ ብቻ እንደሆነ የምጣኔ ሐብት ምሁሩ ጠቁመዋል። ያለፉት ሦስት መንግስታት በእርሻ ላይ ስላልሰሩና በአንጻሩ ደግሞ የህዝብ ቁጥር በጣም እየጨመረ መምጣቱ መሠረታዊ ችግር እንደሆነም አመልክተዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው አለመረጋጋት እና የጸጥታ ችግሮች ነዋሪዎችን ከቀዬቸው እንዲፈናቀሉ የሚያደርግ ሲሆን የጸጥታ ችግር ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ የማይነጣጠሉ ጉዳዮች እንደሆኑ እውነታ ነው። ወቅታዊው የኑሮ ጫና ሌላ ገጽታ የጎዳና ላይ ልመና መስፋፋትም ነው። 

አዲስ ማለዳ በተወሰኑ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች ይኼ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በተመለከተቻቸው ዋጋዎች ጤፍ በኪሎ ከ60 ብር ወደ 150 ብር፣ ዘይት ባለ5 ሊትር 360 ብር የነበረው አሁን እስከ 920 ብር፣ መኮሮኒ በኪሎ ከ16 ብር ወደ 110 ብር፣ ምስር ከ45 ብር ወደ 160 ብር፣ ሽንኩርት ከ25 ብር ወደ 140 ብር በጥቂት ዓመታት ውስጥ መጨመራቸውን ተረድታለች።

እንደ ምጣኔ ሐብት ባለሞያው ገለጻ የጥሬ ገንዘብ ሕትመት መጠንም በዋጋ ንረት ላይ ሚና ያለው ሲሆን በዘመነ ኢሕአዴግ መንግስት በ10 ዓመታት ውስጥ ከምጣኔ ሐብቱ ጋር የማይመጣጠን ህትመት አከናውኖ አጠቃላይ የነበረው ገንዘብ 870 ቢሊየን ብር አድርሶት እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ያለው መንግስትም የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓመታት ቀድሞ ይታተም ከነበረው በሂደት 17 በመቶ ድረስ ዝቅ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም ባለፈው ዓመት የሕትመት መጠኑን አሳድጎ ከቀደመው 29 በመቶ መድረሱን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

“ብር በብዛት ሲታተም ወረቀት ነው የሚሆነው፤ ብር ዋጋ እያጣ እንዲመጣ ያደርገዋል” ያሉ ሲሆን ሌላው ደግሞ ባለፉት ሶስት ዓመታት ብር በመቶ እጥፍ እንዲረክስ ተደርጓል ብለዋል። 

በሌላው ዓለም በዕቃ 10 በመቶ ያተረፈ ነጋዴ በጣም አትራፊ ነው የሚሉት የምጣኔ ሐብት ምሁሩ፤ በጣም አትራፊ የሚባሉት የባንክና የመድህን ዋስትና (ኢንሹራንስ) ዘርፎች እንኳን ትርፋቸው 30 በመቶ እንደሆነ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ላይ “ላስቲክ ከሚሸጠው ነጋዴ ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ መቶ በመቶ ካላተረፈ ያተረፈ አይመስለውም” በማለት በአገሪቱ እየተስተዋለ ላለው የዋጋ ንረት ምክንያቶች መሆናቸውን አጽንዖት ሰጥተዋል። 

95 በመቶ የሚሆነው ገበሬ ዝናብ ጠብቆ ማረሱ እንዲሁም የመስኖ ልማት ተጠቃሚ አለመሆኑ ይታወቃል። “በአገሪቱ መስኖን የሚጠቀመው አራሽ 2 በመቶ ብቻ ነው። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ሳይሰራ የቀረው ይኼ ነው” ሲሉ ባለሞያው ገልጸዋል። 

የዋጋ ንረት መጨመር ዕቅድ ማቀድ እና በበጀት ስራዎችን ማስኬድ እንዳይቻል የሚያደርግ ሲሆን ገንዘብ ያላቸው ሠዎች የዋጋ ንረቱን ለመቋቋም ቤት ወይም መሬት በመግዛት እንዲሁም የውጭ አገራት ባንኮች ላይ በማስቀመጥ “ገንዘባቸውን ከብር ያሸሻሉ”። ይኼ ደግሞ የተጎዳውን ኢኮኖሚ “ያደቀዋል” ተብሏል። 

በምግብ ፍጆታዎች ውድነት ከዚምባብዌ ቀጥሎ በአህጉሩ ሁለተኛ ነን የሚሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ፤ አሁን ካለው የዋጋ ንረት አንጻር “ይኼ ህዝብ ሃይማኖተኛ፣ ታጋሽ፣ ሽብር የሚፈራ ስለሆነ እንጂ እንደዚህ ሕዝብ ማመጽ ያለበት የለም” ሲሉ የዋጋ ንረቱን ጫና አመላክተዋል። 

መንግስት ከሕዝቡ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን እርሻ ሊያስፋፋ እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን መንግስት በአሁኑ ጊዜ ጥረቶች እያደረገ እንደሆነም ይታወቃል። የምጣኔ ሐብት ምሁሩ ዓለማየሁ ገዳ “በእርግጥ እየተሞከረ ነው። እንደሚባለው ባይጋነንም። ተመረተ እንደሚባለው ከሆነ ዳቦ በ12 ብር ሳይሆን በሁለት ብር መግዛት ነበረብን” ይላሉ።

መንግስት በትክክል መፍትሔ የሚፈለግ ከሆነ ሙሉ ትኩረቱን እርሻ ላይ በማድረግ ቅድሚያ ለምግብ ዋስትናው ቢሰጥ የሚፈለገውን ያክል ውጤት ማምጣት ይቻላል የተባለ ሲሆን “በችኮላ ሳይሆን በእርጋታ የታሰበበት እርምጃ እንዲሁም በአንድ ሰብል ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰብሎች ላይ ማተኮር” እንደሚያስፈልግ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ አሳስበዋል።

ባለሞያው “በእኔ መረጃ ከጠቅላላው ሸማቾች ከሚፈልጉት ምግብ የሆኑ ነገሮች መካከል የስንዴ ፍላጎት ያለው አምስት በመቶ ብቻ ነው”  ብለው የገለጹ ሲሆን በአንጻሩ ጤፍ፣ ገብስ እና ማሽላ በርካታውን ስፍራ እንደሚይዙ ተናግረዋል። 

መንግስት ከኢኮኖሚው ጋር የማይጣጣም መጠን ያለው ብር ማተም ማቆም እንዲሁም ብርን የማራከስ ሂደትን መግታት እንዳለበት አሳስበው “ይኼኛው መንግስት ብርን በጣም አርክሷል” ብለዋል።

በከተማዋ ውስጥ ወደ 500 ሺህ ነጋዴዎች እንዲሁም በገጠር 20 ሺህ የሚሆኑ ነጋዴዎች ባሉበት “በእርግጥ ቀላል አይደለም” ቢሉም ነጋዴዎችን መቆጣጠር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ አጽንዖት ሰጥተዋል። 

ዘላቂ መፍትሄዎች እስከሚፈጸሙ ድረስ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በቀበሌ ደረጃ በማውረድ መሠረታዊ የሆኑ ፍጆታዎችን በተሻለ ዋጋ ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ ማስፋት ወሳኝ እንደሆነ ተመላክቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply