የኢትዮጵያ መንግስት የግጭት ማቆም እርምጃ በምዕራባዊን ዓይን…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን አሜሪካና አውሮፓ ህብረት አደነቁ:: የአውሮፓ ህብረት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ መንግስት የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ መዘጋጀቱን ነው የገለጸው፡፡ ህብረቱ አክሎም ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ድጋፉ በፍጥነት እንዲደርስ እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ከመንግስት በኩል እንደተደረገው ሁሉ ከሕወሓት ሃይሎችም የሚጠበቅ እርምጃ እንዳለ አሳስቧል፡፡ ይሄውም ድጋፍ የማጓጓዝ ተግባሩ የተሳለጠ እዲሆን ሲባል ሐወሓት በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣና ዳግም ጥቃት እንዳይፈፅምም ጥሪ አቅርቧል፡፡ አሜሪካ በበኩሏ የኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ሲባል ያስተላለፈውን ውሳኔ አጥብቃ እንደምትደግፍ ገልጻለች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን የመንግስትን አቋም በማድነቅ ውሳኔው በፍጥነት ተግባራዊ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ማለታቸውን አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡ ብሊንከን በመግለጫቸው ውሳኔው የሚጠቅመው በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች ብቻ ሳይሆን በሌላው የሀገሪቱ ክፍሎች ላሉ ሁሉ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ የተወሰደው እርምጃ ጥላቻን ለማስወገድና ሁሉን አካታች ለሆነ ፖለቲካዊ ሂደት መሰረት የሚጥልና ህዝቡም ከደህንነት ስጋት እንዲላቀቅ ትልቅ ፋይዳ አለውም ብለዋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply