የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣በሱዳን ዳርፉርና አብዬ፣ በሶማሊያ፣ … ሰላም ያስከብራል!!! የራሶ አሮባት፣ የሰው ታማስላለች!›› – ፀ/ት ፂዮን ዘማርያም

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣በሱዳን ዳርፉርና አብዬ፣ በሶማሊያ፣ … ሰላም ያስከብራል!!! የራሶ አሮባት፣ የሰው ታማስላለች!››
ለቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ መታወሻ ትሁን!!! ፀ/ት ፂዮን ዘማርያም

UN Peacekeeping Force
‹‹ደግሞ ማወቅ ማለት…..
ከውጭ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን፤ እንዲወጣ ማድረግ….›› ገብረክርስቶስ ደስታ
‹‹ በዘር መደራጀት አይደለም ዘርን መጠየቅ ወንጀል ነው!!!›› ዶክተር አብይ አህመድ ንግግር ከሩዋንዳ መልስ
ከህወሓት ወደ ኦህዴድ ጠቅላይ ጦር ሠፈር የኢትዩጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ጦር ሠራዊት፣አየር ወለድ፣ ዓየር ኃይል፣የፖሊስ ሠራዊት ወዘተ፤ ከላይ ከዋናው ኤታማጆር ጀነራል ሳሞራ ዩኑስ ወደ ጀነራል ሰዓረ መኮንን ተላልፎ በኦህዴድ ጀነራል መኮንኖች የተያዘ ሥልጣን ዕዞች፣ ክፍለ ጦሮች፣ ብርጌዶች፣ ሬጅመንቶች፣ ሻለቃ፣ ሻምበል እስከ ጋንታና እስከ ታች ጓድ ድረስ የሠራዊቱ ዋና ጦር ሠፈር በህወሓትና በኦህዴድ የዘር ሃረግ ስልጣኑ ተይዞል፡፡ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ግዛት የጦር መሳሪያው መከማቸቱ ሆን ተብሎ በህወሓት የተነደፈ የአናሳ ዘውጌኛነት የስነ-ልቦና ደዌ/በሽታ ነው፡፡ ሕወሓት ኢትዩጵያን ካልገዛና ካልመራ ህዝቡ ይበቀለናል በሚል እብሪትና ፍርሃት የተነሳ፤ የክልል ፖሊስ፣ ህዝባዊ ሚሊሽያ፣ ልዮ ኃይል ወዘተ ከፍተኛ ሠራዊትና የመሣሪያ ክምችት በትግራይ ክልል ውስጥ መገኘቱ በትረ-ሥልጣናቸውን በቀጣይና በዘለቄታ ከደደቢት ዋና ጠቅላይ ጦር ሠፈር ለመቆጣጠር የታቀደ ነው፡፡ የኢትዩጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ሬንጀር ዩኒፎርም የሚሠፋው ትግራይ ክልል አልሜዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ነው፡፡ አቦይ ስብሓት ከኤርትራ የመጣውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሲቀበሉና ሲሸኙ ሽምቅ ተዋጊውን ዩኒፎርም አልብሰው፣ መሣሪያ አስታጥቀው፣ ገንዘብ ሰጥተው ተልኮውን በጋራ ነድፈው ለመሆኑ የሚጠራጠር ካለ የፖለቲካን ሀሁ ያልተረዳ ነው እንላለን፡፡ በህወሓት ምክርና ፍኖተ ካርታ የተሠጠው ኦነግ በመላ ኦሮሚያ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ የአማራ፣ ጌዲዬ፣ ሱማሌ፣ ወዘተ ህዝብን ከክልሉ ማስወጥት፣ አዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ማስከበር፣ የወታደራዊና የሲቨል ሥልጣኑን በኦህዴድና ኦነግ ሰዎች የፖለቲካ ሥልጣን መቀራመት ሲሆን፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ ደግሞ ‹‹የኦሮሚያ ኢኮኖሚያዊ አብዬት›› ክልላዊ መንግሥት መር ኢኮኖሚ መዘርጋት፣ በማህበራዊ ጉዳይ የኦሮሚያን ቆንቆ ሁለተኛ የሥራ ቆንቆ ማድረግ፣ የቆንቆ ትምህርት ቤቶች ማስፋፋት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ህወሓትና ኦነግ የተስማሙበት አይነኬ የፍኖተ ካርታው አካል ደግሞ፣ ህገ መንግሥቱን ማስቀጠል፣ አንቀፅ 39 ማሰቀጠል፣ የመሬት ጥያቄ የመንግሥት ሆኖ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ ማድረግ፣ የመለስ ዜናዊ ውርስና ቅርስ የሆነውን ልማታዊ መንግሥት፣ አብዬታዊ ዴሞክራሲና ዘር ተኮር ፌዴራላዊ ሥርዓት ማስቀጠል ስምምነት አድርገዋል፡፡ ለዚህ ነው ኦነግ የኢትዩጵያ መከላከያ ሠራዊት ትብቄ ታጥቆ፣ ቦምብ አገልድሞ፣ ላውንቸር አንግቦ፣ ስናይፐር ይዞ በጠራራ ፀሓይ የህዝብ ልጆች የሚገለው፣ ሴቶች የሚደፍረው፣ ቦንኮች የሚዘርፈው፣ በኦህዴድ ደጀንነት እየተመራ እንደሆነ ያደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ኦነግ የኢትዩጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ሬንጀር ልብስ የሚያገኘው በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው አልሜዳ ጨርቃጨርቅ በ1996 እኤአ በአድዋ ከተማ በኢፈርት የተመሠረተ ድርጁት ነው፡፡ ፋብሪካው ዘመናዊ የጨርቃጨርቅ፣የተለያዩ አልባሳቶች ያመርታል፡፡ ፋብሪካው የጥጥ ማዳወሪያ፣የመፍተያ፣የማቅለሚያና ሁሉን አቀፍ የአልባሳት ማምረቻ ያካተተ ሲሆን የሲዊስ፣ሆላንድ፣የጀርመንና የጣሊያን ስሪት ማሽኖች ተገጥመውለት ነበር፡፡ ‹‹የውጭ አንበሣ፣ ያገር ውስጥ ሬሣ!!!››
• የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ‹‹ያገር ውስጥ ሬሣ፣ የውጭ አንበሣ ›› ከተባበሩት መንግሥታት ተራው ወታደር ከአንድ ሽህ ዶለር በላይ ደሞዝተኛ ሲሆን፣ ጀነራል መኮንኖቹ ደግሞ ከ20 ሽህ ዶላር በላይ በወር ደሞዝ ስለሚከፈላቸው ከሃገራቸው ይልቅ፣ በቅጥረኝነት ዶላር የሚከፍላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ በመሆን ጎረቤት ሃገራትን ይታደጋሉ፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሃገራቸውና ለህዝቡ የገቡትን ቃል ኪዳን መርሳታቸው በተግባር ይገለፃል፡፡ ከ2010 እስከ 2011 ዓ/ም በሃገራችን 3 ሚሊዮን ህዝብ ሲፈናቀል የጦርነት ቀጠና በተባሉት ሱማሌ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ወዘተ እንኮን ይሄን ያህል ህዝብ ተፈናቅሎ አያውቅም እንላለን፡፡
• የኢትዩጵያ የመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (INSA) Information Network Security Agency (INSA) ‹‹ያገር ውስጥ ሬሣ፣ የውጭ አንበሣ ›› ህወሓት/ ኦህዴድ ኢህአዴግ የጦር አበጋዞች መንግሥት በሃገሪቱ ዴሞክራሲን የማስፈን ቁመና መጠበቅ ከእባብ እንቁላል እርግብ መጠበቅ ይሆናል፡፡ ከግንቦት 1983ዓ/ም ጀምሮ በትረ ሥልጣኑን የያዘው የህወሓት/ ኢህአዴግ መንግሥት በብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን ግንባርነት በዘር ላይ የተመሠረተ ህገ-መንግሥት በህዝብ ላይ በመጫን ዘር ተኮር ፌዴራሊዝም በማዋቀር፣ በፌዴራልና በክልል መንግሥታቶች በማዋቀር የዘር ክልሎች ወሰንና ድንበር ያለህዝብ ይሁንታ በማካለል የሃገሪቱን ህዝብ በማያባራ ጦርነት አስገብቶል፡፡ የኢትዩጵያ የመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (INSA)በአዲስ ከተዋቀረ በኃላ በህዝብ መኃል የሚነሱ ግጭቶችና ጦርነቶችን አስቀድሞ መከላከል ሥራ ሲሰራ አልታየም፣ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ የገንዘብ ዝውውር፣ የኦነግ አሸባሪ ጦር፣ የህዝብ ገደላና ማፈናቀል፣ የባንክ ዘረፋ በሃገርና ህዝብ ላይ ሲፈፀም የኢትዩጵያ የመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (INSA)ዝም ብሎ በማየት፣ ኢንሳ መንኮራኩር ወደ ማርስ እያመጠቀ ይመስላል ኢንሣን ‹‹የውጭ አንበሣ፣ ያገር ውስጥ ሬሣ!!!›› ህዝብ የሚለው ለዛ ነው፡፡
የኢትዩጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በአፍሪካ Ethiopia peacekeeping operations in Africa፡- ከሳህራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች በዓለም አቀፍ የሰላም ጥበቃ ወታደራዊ ዘርፍ በአፍሪካ ውስጥ ተሳትፎቸው ከመቸውም ግዜ በላይ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኃላ ከፍ ብሎል፡፡ በልዕለ ሃያላን ሃገራቱም ተሳትፎቸው ትልቅ ድጋፍ፣ ማበረታቻና ድጎማ አስገኝቶላቸዋል፡፡ ለዓለም አቀፍ የሰላም ጥበቃ ከአፍሪካ ሃገራቶች ውስጥ ጥቂት ደሃ ሃገራት ብቻ በብዛት ይሳተፋሉ፡፡ የአፍሪካ መንግስታት የጦር አበጋዞች ፖለቲካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች በተለይ የአህጉሪቱን ፀጥታ ከማስጠበቅ ይልቅ፣ ለአሜሪካና አውሮፓ አገራት ጠላቶች ደረታቸውን ሰጥተው ከሚያገኙት ፍርፋሪ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም፤ ገንዘብ፣ የጦር መሣሪያ፣ ሥልጠና፣ ሌላ ለሃገራቸው ጠላት ነው ያፈሩት፡፡ የጦር አበጋዞቹ መንግስታዊ የሥልጣን መንበራቸውን ዘላቂነትና የግዛታቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ፣ ለልዕለ ሃያላን መንግስታት ቡችላ በመሆን ‹‹ሳይጠሮቸው አቤት ሳይልኮቸው ወዴት!›› በማለት የጌቶቻቸው ጦርነት በሽብርተኝነት ስም አልቃይዳ፣ አልሻባብ፣ አይሲሲ፣ ወዘተርፈ ደረታቸውን ገልብጠው ይዋጉላቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ የሰላም ጥበቃ ለሚሳተፉ የአፍሪካ ደሃ ሃገራት ከፍተኛ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል፡፡ የድንበርና የግዛት ግጭት ያሉባቸው ሃገራት ሉዓላዊነታቸውን ለማፅናትና ለማስጠበቅ ከልዕለ ሃያላን መንግስታት ጋር በመስራት ወሰናቸውን ያፀናሉ፡፡ እንዲሁም የአፍሪካ መንግስታት ውስጣዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበረሰባዊ ችግራቸውን ለመሰወር ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› እንደሚባለው በሃገራቸው የሌለ ሰላምን ከአገራቸው ውጭ ሰላም ለማስከበር ተብለው ይላካሉ፡፡ የልዕለ ሃያላን መንግስታት ጠላቶችን ለመፋለም፤ በቅጥረኛነትና በዘመናዊ የጦር አበጋዝነት ይሰማራሉ፤ ለዚህ ነው፤ የኢትዩጵያ ወታደሮች በሱማሌ፣ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በኮትዲቮር ወዘተ በስመ-ሰላም አስከባሪነት በአብዛኛው ህወሓት ሠራዊት ብቻ የተላኩት፡፡
ኢትዩጵያ በሱዳን ዳርፉር፣ በሰሜንና በደቡብ ሱዳን መሃል በምትገኘው በአብዬ፣ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በጠቅላላው 11,711 ወታደሮችን መንግስት አሰማርቶ እንደሚገኝ የመከላከያ ሚኒስቴሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለፓርላማ ሪፖርት ሚያዝያ 2007 ዓ/ም አቅርበው ነበር፡፡ እንዲሁም በቅርቡ በሶማሊያና በሁለቱ ድንበር 1,374 የሠራዊት አባላት ለማሰማራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውና ከዚህ በፊትም በድምሩ 8,312 ወታደሮች ተመልምለው ሥልጠና መውሰዳቸው ገልጸው ነበር፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እኤአ በ2000 ባወጣው የውሳኔ ሐሳብ ተልዕኮውን ተቀብሎ የሰላም አስከባሪ ኃይል ለሚያሰማራ አገር ወጪውን የሚሸፍን መሆኑን ይገልጻል፡፡ አገሮች ለሚያሰማሩት ሰላም አስከባሪ ኃይል በአገራቸው የደሞዝ ስኬል መሠረት መክፈል የሚኖርባቸው መሆኑን የሚገልጸው የውሳኔ ሀሳብ፣ ሰላም አስከባሪ ላሰማራው አገር በወታደር በወር 1028 ዶላር (20,910 ብር በወር) እንደሚከፈል ያሰረዳል፡፡የአፍሪካ ህብረትም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የሆነ ገንዘብ በዶላር ይከፍላል፡፡ በዚህ ገለፃቸው መሠረት 11,711 ወታደሮች 1,028 ዶላር ሂሳብ 12,038,908 ሚሊዩን ዶላር (244,871,389 ብር በወር) በዓመት ስናሰላው ደግሞ 144,466,896 ሚሊዩን ዶላር በአመት (2,938,456,665 ቢሊዩን ብር) እንደሚከፈል ያሳያል፡፡ ታዲያ ለወታደሩ በአገሩ የደሞዝ ስኬል መሰረት ከተከፈለው ቀሪውን ገንዘብ የህወሓት የጦር አበጋዞች እንደሚቀራመቱት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ የወታደር ደሞዝ ሲሆን የጀነራል መኮንኖች ደሞዝ በወር 20 ሽህ ዶላር (400,000ብር በወር)፣የበረሃ አበል ከቤተሰብ በመለየት የሚደረግ ድጎማ በቀን 600 ዶላር በወር 18000 ሽህ ዶላር (360,000) እንዲሁም የህይወት ኢንሹራንስና ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ያገኛሉ፡፡ ኢትዩጵያ በሱዳን ዳርፉር፣ በሶማሊያና በሁለቱ ሱዳኖች ሰላም አስከባሪዎች ተልዕኮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት የጥምረት ተልዕኮ ከተቀበለቻቸው ለሰላም አስከባሪ ኃይል ከሚሰጥ ክፍያ ከሶስት ቢሊዩን ብር በላይ በዓመት ታገኛለች፡፡ ተመድ ለሰላም አስከባሪ ኃይል ከሚከፍለው በተጨማሪ ለሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ በኪሎ ሜትር የሚከፍል መሆኑን መረጃው ይጠቁማል፡፡ በ2005 ዓ/ም የተሸሻለው የመከላከያ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር በዓመት ከፌዴራል መንግስት ከሚያገኘው በጀት በተጨማሪ፣ ከሰላም ማሰከበርና ከኢትዩጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የንግድ ድርጅቱ ትርፍ መንግስትን እያስፈቀደ እንዲጠቀም ይፈቅድለታል ብለው ነበር አሻንጉሊቱ ሚኒስትሩ፡፡ የኢትዩጵያ የመከላከያ ኃይል የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በሰው ኃይል ላይ ብቻ ተመስርቶ የነበረው ስምሪት እየተስፍፍ መጥቶ በተለያዩ የድጋፍ ሰጪዎች ገንዘብ ማስገኛ ጭምር እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የወያኔ የጦር አበጋዞች መንግስት በዳርፉር ተወጊ ሄሊኮፕተሮች እንዲሰማሩ አድርገዋል፡፡በአብዬና ደቡብ ሱዳን ታክቲካል ሄሊኮፕተር በማሰማራት ተጨማሪ ዶላር ይገኛል፡፡አገሪቱ የተለያዩ ሎጅስቲክስ እያቀረበች የመከላከያ ኃይል ወደ መከላከያ ንግድ እየገባ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የውሃ ኢንጅነሪንግ ሥራም እየተኮናተረ በመስራት ላይ ይገኛል ይላሉ ኮሎኔል ነጋሽ ህሉፍ፡፡ የወያኔ የጦር አበጋዞች መንግስት፤ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን እንደ ንግድ በመቁጠር በሩዋንዳ፣በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሱዳን ዳርፉር፣ በደቡብ ሱዳንና በሰሜን ሱዳን መካከል በሚገኘው በአብዬ ግዛት፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ተልዕኮውን እየፈፀመ እንደሚገኝና ዳጎስ ያለ ዶላር እንደሚያግበሰብስ የአደባባይ ሚስጢር ሆኖል፡፡ታዲያ ለኢትዩጵያ የመከላከያ ኃይል ፀባቸው ቢቀጥልለት ይሻለዋል ወይስ ሰላም ቢወርድ ፍርዱን ለአንባቢ ትተናል፡፡ለዚህ ነው የኢትዩጵያ የመከላከያ ኃይል የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጎረቤቶቻችን አይግቡብን የሚል ተቃውሞቸውን በየቦታው የሚያሰሙት ሃገራችን በዚህ ያልተቀደሰ ሥራዋ ሃገራችን ብዙ ጠላት እንደምታፈራ ምንም ጥርጥር የለውም እንላለን፡፡ ለዚህ ነው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኢህአዴግ እንዲሁም ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደኢህዴን ክልላዊ የጦር አበጋዞች መንግስት በልማታዊ መንግስት ስም መንግሥት መር ኢኮኖሚና ኢፈርት፣ ጥረት፣ ዲንሾና ወንዶ የፓርቲ የንግድ ድርጅቶች በመፈልፈል የግሉ ዘርፍ እንዳይሰራ በማድረግ ህዝቡ በምግብ ራሱን እንዳይችል በማድረግና 3 ሚሊዮን ህዝብ ከቀየው እንዲፈናቀል በማድረግ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ፈፅመዋል፡፡
• በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን፣ የማንነት ጥያቄ ሠለባዎች፣ ባለፉት 27 አመታት ወያኔ ባጸደቀው በዘርና ልሳን በተከለለ ፌዴራላዊ ክልላዊ አስተዳደር የተነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁም ስቅሉን በማየት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ በወያኔ ከፋፍለህ ግዛው የአባላህኝ ዘመን ከክልላቸችን ውጡ፣ ቅስቀሳ የተነሳ የሃገራችን ዜጎች በሁሉም የሃገሪቱ ግዛት ውስጥ ተዘዋውሮ የመስራት መብቱንና ክብሩን አጥቶል፡፡ በዚህም የተነሳ ከአንድ ሚሊዩን 500 ሽህ ህዝብ በላይ የኦሮሞና ሱማሌ ህዝብ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በጉጂ ኦሮሞዎችና በሲዳማ ጊዴኦ የዘር ግጭት የተፈናቀሉ ከ750 ሽህ እስከ አንድ ሚሊዮን ወገኞቻችን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በሲዳማና ወላይታ በተከሰተው የዘር ግጭት ከ20 እስከ 30 ሽህ ህዝብ ሲፈናቀል በተመሳሳይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 8510 የትግራይ ተወላጆች የዘር ግጭትን በመፍራት ወደ ትግራይ ክልል ተመልሰዋል፡፡ በአጠቃላይ በሃገሪቱ 3 ሚሊዮን ህዝብ ከቀየው ተፈናቅሎ ይገኛል፡፡
• የህወሃት የመከላከያ ሠራዊት አመታዊ በጀት፡-ወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት በ2007ዓም ዓመታዊ ባጀት 178.6 ቢሊዩን ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለመከላከያ 8.1 ቢሊዩን ብር በጀት ተመድቦል፡፡ የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከሃገሪቱ ባጀት ከተመደበላቸው ዋናዎቹ አራቱ ፊዴራል ቢሮዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሚገርመው አዲሱ የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንደ አሜሪካው መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን ህንፃ አምስት ክንፍ አምሳያ ያለው ንድፍ እንዳለው ተውቆል፡፡ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ፣የሃገር መከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አዲስ ሕንፃ ዋና ቢሮ በ1.3 ቢሊዩን ብር ለመገንባት ኮንትራት ያለ ጨረታ ወስዶል፡፡ የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ዋና ቢሮ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ፊት ለፊት እየተገነባ እንደዳለ ይታወቃል፡፡ ወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት በ2008ዓም ዓመታዊ ባጀት 223.3 ቢሊዩን ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለመከላከያ 9.5 ቢሊዩን ብር በጀት ተመድቦል ነበር፡፡ ህዝብ በሚከፍለው ግብር ደሞዝ የሚከፈለው መከላከያ ሠራዊት፣በሃገሪቱ 3 ሚሊዮን ህዝብ ከቀየው ሲፈናቀል መከታና አሌንታ አለሆነውም፡፡
• የህወሃት የመከላከያ ሠራዊት ጦር አበጋዞች የብሄር ብሄረሰብ ተዋፅኦን በተመለከተ፡- የህወሃት መከላከያ ሠራዊት፣ጦር አበራዞች ከላይ ከዋናው ኤታማጆር ጀምሮ ዕዞች፣ ክፍለ ጦሮች፣ ብርጌዶች፣ ሬጅመንቶች፣ ሻለቃና፣ ሻምበል ድረስ የሠራዊቱ ዋና ጦር ሠፈር በትግራይ ህወሓት የዘር ሃረግ ወደ ኦሮሚያ ኦሀህዴድ የዘር ሃረግ የፈረቃ ስልጣኑ የተያዘ መሆን ዳክተር አብይ አህመድ መንግሥት ታሪካዊ ስህተት ከመድገም ማረም የተሸለ መሆኑን በጊዜው እንመክራለን፡፡ በትግራይ ክልል የሚደረግ ልዩ የፖሊስ፣ ህዝባዊ ሚሊሽያ፣ የፖሊስ ሠራዊት፣ የጦር ሠራዊት ወዘተ እንዲሁም የጦር መሳሪያው መከማቸቱ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ ወዘተ ክልሎችም ተመሳሳይ የሠራዊት ምልመላና የመሣሪያ ክምችት ሃገርና ህዝብን ወደማያባራ የዘር ጦርነት ከመዝፈቁ ውጪ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለው የወንድማማች ጦርነት ከንቱ ነው እንላለን፡፡ ትላንት በኢትዮጵያና ኤርትራ የተደረገው የበድማ ጦርነት ከ70 እስከ 100 ሽህ ወገኖቻችንን አጥተናል፡፡ እንዲህ አይነት የቂሎች ጦርነት ‹‹መቼም የትም አይደገም›› ማለት ሲገባን ዛሬም በወልቃይት፣ በራያ፣ ወዘተ የሚደረግ የጦርነት ቀረርቶ በሽማግሌዎች በሰላም እንዲፈታ እንመክራለን፡፡ ወያኔ ኢትዩጵያን ካልገዛና ካልመራ ህዝቡ ይበቀለናል በሚል እብሪትና ፍርሃት የተነሳ፤ የኢትዩጵያ መከላከያ ሠራዊትና የመሣሪያ ክምችት በሙሉ በትግራይ ክልል ውስጥ መገኘቱ በትረ-ሥልጣናቸውን በቀጣይና በዘለቄታ ከደደቢት ዋና ጠቅላይ ጦር ሠፈር ለመቆጣጠር የታቀደ የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር ተላላኪነት የሚፈፀም ተልዕኮ አንድ የሰሜን ሸዋ ገበሬ እንዳሉት ‹‹በብረት የመጣ በብረት ነው የሚመለሰው!!!›› እንዳሉት ሁሉም ቤት እሳት አለ ይሄም ወደ ዘር ግጭት ያመራል፡፡
• የኢትጵያ ኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት ከደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ ለሌሎች አጎራባች አገሮች ሸጦ የውጭ ምንዛሪ ለማገግኘት የሚሠራ የሀገራችንን ህጻናትና ተማሪዎች እንዳያጠኑ በድቅድቅ ጨለማ የሚያኖረው የህወሓት/ ኦህዴድ ኢህአዴግ መንግሥት ጸረ ህዝብ አቆም እንደቀጠለ ነው፡፡ የእኛ አገር መንግሥታዊ ተቆማት መከላከያ ሠራዊቱ መብራት ኃይል የጎረቤት አገራትን ለማገልገል የተዋቀሩ መስሪያ ቤቶች መሆናቸው ህዝብ በከፈልንው ግብርና ታክስ የኤሌትሪክ አገልግሎት እያገኘ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡
• የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በሃገራቸውና በወገናቸው ጉዳይ ስለሚያገባቸው የዶክተር አብይ አህመድ መንግሥት ጥሪ አለማድረጉ በዘርና በዜግነት የተደራጁ ነፃ አውጪዎች ወደ ሀገር እንዲገቡ ሲደረግ ለእነሱ ጥሪ አለመቅረቡና በተማሩት የወታደራዊ ሳይንስ እዉቀት አገራቸውን እንዳያገለገሉ አለመጋበዛቸው ከኮነሬሉ አይጠበቅም እንላለን፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ሃገራቸውን የማገልገልና ከወገናቸው ጋር በሃገራቸው የመኖር መብት አላቸው እንላለን፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በሃገራቸው የሌለ ሰላምን፣ በአጎራባች አገራት ሰላም ለማስከበር ይማስናሉ!!!
‹‹በብረት የመጣ በብረት ነው የሚመለሰው!!!›› የሰሜን ሸዋ ገበሬ የተገኘ ጥቅስ!!!
ኦህዴድ‹‹የውጭ አንበሳ፣ የውስጥ ሬሳ!!! ‹‹ኦነግ አባ ቶርቤ!!!››

Leave a Reply