የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ባደረገው ቁጥጥር 9 ተቋማት ላይ የማሸግ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

ባለስልጣኑ በበዓል ሰሞንበ3 መቶ 23 ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደወሰደ እና ከነዚህም መካከል ለ3 መቶ 14 ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱንም ለኢትዮ ኤፍ ኤም ገልጿል።

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የምግብ እና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር እስጢፋኖስ ጌታቸው ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት በሁሉም ክፍለ ከተሞች በጥቅሉ 2 ሺ 3 መቶ 76 የምግብና ጤና ነክ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም የተለያዩ ባዛር ቦታዎች ላይ ቁጥጥር ስራ መስራታቸውን አንስተዋል፡፡

ቁጥጥር ከተደረገባቸው ክፍለከተሞች መካከል አራዳ፣ ንፋስ ስልክ፣ አዲስ ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማ እና ጉለሌ ክፍለ ከተማ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ከተገኙት መካከልም 4ሺ 7 መቶ 25 ኪሎ ግራም የተበላሹና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው እንዲሁም ባልተገባ ሁኔታ ሲቀየጡ የተገኙ ምግቦች እና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው 338 ሊትር መጠጦች እንዲወገዱ መደረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

የካ ክፍለ ከተማ አካባቢም ማር በየሰፈሩ በባሊ ይዘው በሚዞሩ ግለሰቦች ማር ያልሆነ ምንነቱ ያልታወቀ ነገር ይዘው በመገኘታቸው ግለሰቦቹ አሁን ድረስ በህግ ቁጥጥር ስር እንሚገኙ ተናግረዋል።

ማህበረሰቡም ከእንደዚህ አይነት ቦታዎች ከመግዛት መቆጨብ እንዳለበት ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
እንደ አጠቃላይ በበዓላት ወቅት በርካታ በምግብና መጠጥ እንዲሁም በጤና ነክ ምርቶች ላይ ያልተገባ ጥቅም ፈላጊ ግለሰቦች በሚፈጥሩት ችግር ምክንያት ህብረተሰቡን ተላላፊ ለሆኑና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋልጠው የራሳቸውን ኪስ የሚያካብቱት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እርምጃ እየወሰድን እንገኛለን ብለዋል።

በሐመረ ፍሬው

ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply