የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ )በሀገር ውስጥ በሴቶችና በሕፃናት የመነገድ ድርጊት ላይ ያተኮረ የክትትል ሪፖርት በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።

ይህ የክትትል ሪፖርት በሀገር ውስጥ በሴቶች እና በሕፃናት መነገድን የመከላከል፣ ለተጎጂዎች የሚደረጉ ጥበቃ ፤ መልሶ ማቋቋምን፣ እና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የተወሰዱ እርምጃዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በሃገራችን ውስጥ በሰዎች የመነገድ ድርጊት መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ናቸው ተብለው የሚታወቁ ቦታዎችን አስቀድሞ የመለየት ስራ መሰራቱ ተገልጿል፡፡

በመጀመሪያ ዙር በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ እና በአፋር ክልል በሰመራና ሎጊያ ከተሞች፤ በሁለተኛ ዙር በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ እና በቀድሞ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአሁኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ወላይታ ዞን፣ ከኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን፤ በአዳማ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ቢሮዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የፌዴራል ተቋማት ኮሚሽኑ ክትትል ማድረጉን በሪፖርቱ አስታውቋል።

በዚህም 23 የክልል ቢሮዎች፣ 6 የፌዴራል ተቋማት፣ 4 የከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች፣ 14 የዞን መምሪያዎች እና የፖሊስ ጣቢያዎች፣ 13 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች፣ 4 የሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች እንዲሁም 21 የድርጊቱ ተጎጂዎችን ማነጋገር እና የተጎጂ ታሪኮችን መመልከት መቻሉን ኢሰመኮ ገልጿል፡፡

በክትትሉም ሴቶች እና ሕፃናት በሀገር ውስጥ በሰው መነገድ ድርጊት ሳቢያ ከጾታዊ እና ከአካላዊ ጥቃት እንዲሁም ከአድልዎና መገለል የመጠበቅ መብቶቻቸው፣ እንደተጣሱ አመላክቷል።

ኮሚሽኑ በግኝቱም እስካሁን የተሰሩ ስራዎች ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ከሀገር ውጪ በሰው የመነገድ ድርጊት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸው በሪፖርቱ ጠቅሷል።

ያሉትን የመብት ጥሰቶች በተናጠል እየመረመሩ ለእያንዳንዱ ሕገ ወጥ ድርጊት ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ይልቅ በአንዱ የጥቃት አይነት ላይ ብቻ ምርመራ በማካሄድ ክስ እንደሚቀርብ እና በዚህም አጠቃላይ የክስ ምጣኔው ዝቅተኛ መሆኑ አብራርቷል፡፡

መንግሥት በሀገር ውስጥ በሰው መነገድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲችል፤ ሕፃናት ወደ ከተሞች በመፍለስና በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ለብዝበዛ የሚዳረጉበትን ሁኔታ ለመቀነስ የሚያስችል ዝርዝር ምክረ ሐሳብም አቅርቧል።

የሲቪል ማኅበራትም በሰው የመነገድ ድርጊት ተጎጂ ለሆኑ ሴቶችና ሕፃናት የመጠለያ፣ የማኅበራዊ ሥነ ልቦና ድጋፍና የሕግ ምክር አገልግሎት እንዲሁም የሥራ ክህሎት ስልጠና እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

የኮሚሽኑ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሸነር ርግበ ገብረሐዋርያ፣ በሀገር ውስጥ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ነገሮች ሰፊ እና ውስብስብ በመሆናቸው ሁሉን አቀፍ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ማኅበራዊ ስልቶች መነደፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

አክለውም በሴቶች እና በሕፃናት የመነገድ ወንጀልን የመከላከል፣ ለተጎጂዎች ድጋፍ እና ጥበቃ የማድረግ እንዲሁም ወንጀሉን የመመርመርና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት የማረጋገጥ እርምጃዎች ከሀገር ውጪ ለሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገር ውስጥ በሰው መነገድ ድርጊት ላይም ትኩረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

እነዚህንም ለመተግበር የሚዘረጉ የትብብር ማዕቀፎች በሁሉም ባለድርሻ አካላት ተነሳሽነት እና ትብብር መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

መሳይ ገብረ መድህን
ታህሳስ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply