የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስተካከያ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጠየቀ

ማክሰኞ ኀዳር 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በኩል ባወጣው መግለጫ በወልቃይት ጠገዴ ስቲት ሁመራ ዞን በጎንደር ዲስትሪክት በኩል ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት “በሽሬ ዲስትሪክት” ተብሎ በመጠራቱ ማስተካከያ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጠየቀ።

ባንኩ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ፤ በህዳር 3 ቀን 2015 በግጭት ቀጠና የነበሩ ቅርንጫፎቹ ጋር ተያይዞ በቀረበው ዜና ላይ የመረጃ ክፍተት ስለተስተዋለ ማስተካከያ እንዲደረግለት ጠይቋል።

በዚህም፤ የባንኩ ቅርንፎች የሆኑት ሁመራ፣ ቃፍታ፣ ዳንሻ፣ ማይካድራ፣ አዉሮራ፣ ኣዲረመጽ እና ከተማ ንጉስ በቅርቡ ሥራ እንደገና የጀመሩ መሆናቸዉን ተብሎ የተላለፈዉ መረጃ ስህተት መሆኑን ገልጿል።

”ከላይ የተዘረዘሩት ቅርንፎች ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት በአካባቢዉ ከሚገኙ የአስተዳደር አካላት በተደረገ ከፍተኛ ድጋፍ እና ትብብር በጎንደር ዲስትሪክት አማካኝነት እንደገና ተከፍተዉ ለህብረተሰቡ አልግሎት እየሰጡ የቆዩ እና አሁንም አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ቅርንጫፎች መሆናቸዉን እንገልጻለን“ ብሏል ባንኩ በደብዳቤው።

በተጨማሪም በሁመራ እና በአካባቢዉ የሚገኙ አዲሀር፣ በአከር ፣ማይጠብሪ፣ ማይጋባ፣ ቆራሪት፣ ተከዜ፣ ሰቲት፣ አዲጎሹ እና አደባይ ቅርንጫፎች ከአካባቢዉ አስተዳደር ጋር በመሆን በጎንደር ዲስትሪክት በኩል አስፈላጊዉን ግብዓት በማሟላት እንደገና በመክፈት ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፌዴራል ተቋም አንደመሆኑ መጠን ኹሉንም የባንኩን ዲስትሪክቶች ስያዋቅር የክልሎችን የአስተዳደር ወሰን ተከትሎ ሳይሆን፤ ለባንክ አሰራር አመቺ የሆነዉን መንገድ ብቻ በመከተል ያደራጀን መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወልቃይት ጠገዴ ስቲት ሁመራ ዞን በጎንደር ዲስትሪክት በኩል ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት “በሽሬ ዲስትሪክት” ተብሎ መጠራቱ ቅሬታ እንደፈጠረበት በመግለጽ በአስቸኳይ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ዞኑ መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል።

The post የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማስተካከያ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጠየቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply