የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲስተም ችግር በገጠመው ወቅት ገንዘብ የወሰዱ ግለሰቦች እስከዚህ ሳምንት መጨረሻ ድረስ የማይመልሱ ከሆነ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው አስታወቀ።

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ለቢቢሲ ኒውስ ዴይ ሲናገሩ የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞች እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ካልመለሱ ማንነታቸውን ለፖሊስ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።

“በዲጂታል ነው ዝውውር የፈጸሙት። ደንበኞቻችን ስለሆኑ እናውቃቸዋለን።

የፈጸሙት ተግባር በሕግ ያስጠይቃቸዋል። ለፖሊስ ማንነታቸውን እናሳውቃለን” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከገንዘብ ዝውውር ሥርዓቱ ማሻሻያ ሂደት ጋር በተያያዘ አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ምሽት ችግር ባጋጠመው ወቅት በርካታ ደንበኞች በሂሳባቸው ካለው ገንዘብ በላይ ዝውውር ማድረጋቸው ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት እንደሚሉት ከሆነ አብዛኞቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሆኑ ደንበኞች የተከሰተው ችግር ሲያጋጥም ባንኩ የሳይበር ጥቃት የደረሰበት መስሏቸው ገንዘብ ቢያዘዋውሩ ማንነታቸው የሚታወቅ አልመሰላቸውም ነበር።

አቶ አቤ “አሁን የፈጸሙት የገንዘብ ዝውውር በመታወቁ የወሰዱትን ገንዘብ በራሳቸው እየመለሱ ያሉ አሉ” ብለዋል።

በተፈጠረው ችግር ወቅት የማይገባቸውን ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞቹ እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ እንዲመልሱ የጠየቁት አቤ ሳኖ፤ ይህ ካልሆነ ግን ክስ ተመስርቶ ግለሰቦቹን ማንነት ለፖሊስ አሳልፎ እንደሚሰጥ አስጠንቅቀዋል።

ማንነታቸውን ለፖሊስ አሳልፋችሁ መስጠታችሁ ከደንበኞቻችሁ ጋር ያላችሁን ግንኙነት አያበላሽባችሁም ወይ ተብለው የተጠየቁት አቤ ሳኖ፤ “ከሌቦች ጋር ስለምን ዓይነት ግንኙነት ነው የምናወራው?” ብለው ጠይቀው፤ “በሂሳባቸው የሌላቸውን ገንዘብ ነው የወሰዱት።

የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ እንደወሰዱ በጣም እርግጠኛ ነን” ሲሉ መልሰዋል።

ባንኩ አርብ መጋቢት 6/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ የሲስተም ችግር በገጠመው ወቅት የተወሰደበት ገንዘብ 2.4 ቢሊዮን ብር (40 ሚሊዮን ዶላር) መሆኑን አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቦ ነበር።

ባንኩ የተወሰደበትን ትክክለኛ የገንዘብ መጠን በቢቢሲ የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ የኦዲት ምርመራው ባለመጠናቀቁ የተወሰደውን ገንዘብ መጠን አሁን ላይ አይታወቀም ብለዋል።

መጋቢት 11ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply