የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክርቤት የዘንድሮው የሃጅን ጉዞ በዶላር እጥረት ምክንያት ባሰበው ልክ ሃጃጆችን መሸኘት እንዳላስቻለው አስታወቀ፡፡የምክርቤቱ ፕሬዝደንት ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሓ…

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክርቤት የዘንድሮው የሃጅን ጉዞ በዶላር እጥረት ምክንያት ባሰበው ልክ ሃጃጆችን መሸኘት እንዳላስቻለው አስታወቀ፡፡

የምክርቤቱ ፕሬዝደንት ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሓጂ ዑመር እድሪስ እንዳስታወቁት፣ ከሆነ የሃጅ ጉዞ ስነስርአት ከዚህ ቀደም ለሃገራችን ይሰጥ ከነበረው የተጓዦች ብዛት ተጨማሪ ተፈቅዶ የነበረ ቢሆንም በዶላር እጥረት ምክንያት ተጓዦችን መላክ አልተቻለም፡፡

የሳዉዲ መንግስት ከዚህ ቀደም ለሃገራችን ይሰጥ ከነበረው የሑጃጆች ቁጥር ጨምሮ ፈቃድ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም እንደ ሃገር ባጋጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ 3ሺህ ሑጃጆችን ለመላክ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር አክለውም ተጨማሪ 1ሺህ ተጓዦችን በተጠባባቂነት መያዛቸውን ያስታወቁ ሲሆን ከ4ሺህ በኋላ ያሉ የሃጅ ጉዞ ተመዝጋቢዎች ገንዘባቸው በየባንኩ ወደአካውንታቸው እንደሚመለስም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክርቤት ፕሬዝደንት ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሓጂ ዑመር እድሪስ ከሰሞኑ በሃገራችን የተከሰተውን የበርካቶች ጭፍጨፋን ያወገዙ ሲሆን በተለይም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ደም ማፍሰስ በጣም አሳፋሪ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡

‹መጅሊሳችን አዝኗል› ያሉት ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር እድሪስ የሰው ልጅ በሰውነቱ ያለምንም ተጨማሪ መመዘኛ ሊከበር እንጅ እና የመኖር መብቱ ላይ አደጋ ሊደቀን አይገባም ብለዋል፡፡
የምክርቤቱ ፕሬዝደንት ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር አክለውም በጅምላ ጭፍጨፋ እና የንጹሃን ደም መፍሰስ ሁሉንም ሊያሳስብ ይገባል ያሉ ሲሆን በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትም ከተጨማሪ ጥፋት እና ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ‹ለእናንተም አይጠቅማችሁም ፣ መፀፀት አለባችሁ › ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ህጉን ጠበቅ እንዲያደርግ፣ የህዝቡን ሰላም እና ደህንነትን የማስጠበቅ ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባውም ሙፍቲህ ሓጂ ኡመር እድሪስ አሳስበዋል፡፡
ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የደረሰው አይነት የንጹሃን ጭፍጨፋ እና ግፍ መድሃኒቱ የማይታወቅ በሽታ፣ ድርቅ እና ርሃብ ያመጣብናል ያሉት ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር ‹ተያይዘን ከማለቅ እና ከመጨነቅ ሁሉም ቢያስብበት እና ወደሰላም ብንመለስ› ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በአብዱሰላም አንሳር
ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply