የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሊቃነ ጳጳሳቷ አስቸኳይ ጥሪ አቅርባለች፡፡ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ ተሰጥቷል የተባለውን የጳጳሳት ሹ…

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሊቃነ ጳጳሳቷ አስቸኳይ ጥሪ አቅርባለች፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ ተሰጥቷል የተባለውን የጳጳሳት ሹመትን በተመለከተ የቤተክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ጥሪ አቀረቡ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ብፁዕ አቡነ አብርሃም እሁድ ከሰዓት በኋላ በቤተክርስቲያኗ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው ስለተከሰተው ሁኔታ ለመነጋገር በተለያዩ አካባቢዎች ላሉ ጳጳሳት፣ ለመንግሥት እና ለምዕመናን ጥሪ አቅርበዋል።

አቡነማቲያስ እሁድ ጥር 14/2015 ዓ.ም. ጠዋት ተሰማ ባሉት “ሕገ ወጥ ሲመተ ጳጳሳት” ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጪ በሕገ ወጥነት የተከናወነ መሆኑን በመግለጽ በዚህ ዙሪያ ቤተክርስቲያኗ የምትወስደውን ቀጣይ እርምጃ በተመለከተ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት፡-

1.በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት በአስቸኳይ ወደ መንበረ ፓትርያርክ እንዲመጡ ጥሪ ቀርቧል።

2. መንግሥት ክስተቱ በሀገር ላይ ጭምር የሚያስከትለውን ጉዳት ተመልክቶ በጉዳዩ ላይ ሕጋዊ ሓላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
3. ምዕመናን ቤተክርስቲያንን ከመቸውም ጊዜ በላይ በንቃት በሀሣብና በጸሎት እንዲጠብቁ ቅዱስነታቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በትናንትናው እለት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ህገወጥ በተባለው “የጳጳሳቱን የሹመት ሥነ ሥርዓተ” የሚያሳዩ እና “አዲስ ተሾሙ የተባሉትን ጳጳሳት” የሚያሳዩ ፎቶግራፎች በስፋት ሲዘዋወሩ ታይተዋል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በዘር ለመክፈል የተኬደው ርቀት አደገኛም አሳዛኝም ነው” በማለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

አክለውም “ሕገ ወጥ የጳጳሳት ሹመት ገጠር ውስጥ ተደብቆ በመፈጸም ታሪክ ይቅር የማይለው ኃጢአት ተሠርቷል” ክስተቱን ለማስቆም የሚችሉ አካላት “ለማስቆም ባለመፈለጋቸው በሰማይም በምድርም ተጠያቂ ናቸው” ሲሉ በውል ያልጠቀሷቸውን አካላት ወቅሰዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የመንግስት ኮሚንኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ለገሰ ቱሉ ይህን ብለዋል።

”የአንድ ማህበረሰብ ወይም ሀገር ህዝቦች ህግና ስርዓት የሚመነጩት ከሰው ልጆች የዕድገት ደረጃ ፣ ንቃተ ህሊናና ማህበራዊ ስነ-ልቦና ፣የህዝቡ ፍላጎትና መሻት፣ እምነትና ቀኖና ነው።

ከምድራዊም ሆነ መንፈሳዊ ህግ፣ ስርአት፣ ትውፊትና ቀኖና ጋር የሚጋጭ የትኛውም ድርጊት መጨረሻው የሰመረ ሊሆን አይችልም።

ከክፍፍል ይልቅ አንድነትን፣ ከጥለቻ ይልቅ ፍቅርና ይቅርባይነትን መርህ አድርገን በሚንቀሳቀስበት ወቅት ከአንዱ የቤተክህነታችን ክፍል ዛሬ የሰማነው ድርጊት አሳዛኝ ዜና ነው።

አባቶች በትዕግሥት እና ሃይማኖታዊ ስርዓት ችግሩን ይፈታሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ጉዳዩን የተለያየ ፖለቲካዊ እና አካባቢያዊ ገፅታ መስጠትም ተገቢ አይደለም።

የእምነቱ ተከታይ አባቶች ሁኔታውን በስክነትና ቤተ-ክህነታዊ ስርዓት እንዲፈቱ ጉዳዩን ለነሱ መተው እጅጉን አስፈላጊ ነው።” ብለዋል።

ኢትዮ አፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
Twitter https://twitter.com/EthioFM
YouTube https://www.youtube.com/…/UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/videos
Facebook https://www.facebook.com/onelovebroadcast
Website https://ethiofm107.com/
ያሎትን አስተያየት እና ጥያቄ በአጭር መልዕክት 6321 ላይ ይላኩልን።
ከኛ ጋር ስለሆናችሁ ከልብ እናመሰግናለን።

Source: Link to the Post

Leave a Reply