የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ 185 አባላቱ ያለ በቂ ምክንያት መታሰራቸውን አስታወቀ፡፡ኢዜማ ይህንን የገለጸው የዜጎች የሰላም ደኅንነት፣ የሰዎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይዞታ፣…

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ 185 አባላቱ ያለ በቂ ምክንያት መታሰራቸውን አስታወቀ፡፡

ኢዜማ ይህንን የገለጸው የዜጎች የሰላም ደኅንነት፣ የሰዎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይዞታ፣ እንዲሁም በአገሪቱ የተከሰቱትን ግጭቶችና ድርቅ አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

መንግሥት የጠራ አቋም ይዞ ሰላም ባለማስከበሩ ምክንያት ዜጎች በተለያዩ አካባቢዎች እየሞቱና ለእስር እየተዳረጉ መሆኑን፣ ኢዜማ በተጨባጭ ለመለየት መቻሉን አስታውቋል፡፡

መንግሥት ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ አፅንኦት ሰጥቶ መከታተል እንዳለበት የገለጸው ፓርቲው፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች ያለ ምንም ምክንያት ታፍሰው ለእስር መዳረጋቸውን ካሰባሰብኩት መረጃ ለማወቅ ችያለሁ ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መሆናቸውን፣ መንግሥትም ሰላምን ለማስፈን የሚያደርገው ጥረት ቁርጠኝነት የሚታይበት እንዳልሆነ የኢዜማ ድርጅት ጉዳይ መምርያ ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት፣ ድርቅና ሌሎች ችግሮች የተፈጠሩት ከሰላም ዕጦት እንደሆነ ኃላፊው ጠቅሰው ሰላም ሳይኖር ስለልማት፣ ስለኢኮኖሚና ስለዴሞክራሲ ማውራት ከቅንጦት እንደማይተናነስ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት የማይችሉበት፣ ሃይማኖታዊ በዓላትን እንኳን ማክበር የተቸገሩበት ሁኔታ መፈጠሩን አክለው ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የተከሰቱ አንዳንድ ኩነቶችም ቢታዩ ዜጎች ምን ያህል በአስጨናቂ የሰላምና ደኅንነት ዕጦት አደጋ ውስጥ እንዳሉ መገንዘብ እንደሚቻል፣ ለአብነትም በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎችና በሌሎች አካባቢዎች ግጭት በመፈጠሩ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ወደ ሰላም መቀየር ካልተቻለ አሸናፊ እንደሌለ ገልጸው፣ መንግሥት በዘፈቀደ ግጭቶችን አስቆማለሁ ካለ የበለጠ እንደሚስፋፉ ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት በኃይል ግጭትን መፍታት እንደማይችል ከዚህ በፊትም የነበረው ግጭት ማሳያ እንደነበር የገለጹት አቶ ዋስይሁን፣ እስካሁን የተከፈለው ዋጋ እንደሚበቃና መንግሥት ችግሮችን በድርድር መፍታት አለበት የሚል አቋም ፓርቲው መያዙን ተናግረዋል፡፡

(ሪፖርተር)

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

Twitter https://twitter.com/EthioFM

YouTube https://www.youtube.com/@onelovebroadcast/videos

Facebook https://www.facebook.com/onelovebroadcast

Website https://ethiofm107.com/

Source: Link to the Post

Leave a Reply