የኢትዮጵያ የኃይል እጥረት ኬንያ ስምምነቷን እንድታሻሽል እያስገደዳት ነዉ ተባለ፡፡ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችዉን የ25 ዓመት የሃይል ግዢ ስምምነት መልሳ ለማጤን መገደዷ ተገልጿል፡፡የኬንያ…

የኢትዮጵያ የኃይል እጥረት ኬንያ ስምምነቷን እንድታሻሽል እያስገደዳት ነዉ ተባለ፡፡

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችዉን የ25 ዓመት የሃይል ግዢ ስምምነት መልሳ ለማጤን መገደዷ ተገልጿል፡፡

የኬንያ የነዳጅ እና ኢነርጂ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን በኢትዮጵያ ከፍ እያለ የመጣዉ የሃይል ቀዉስ ለናይሮቢ አደጋ የደቀነ ነዉ ያለ ሲሆን፤ ሁለቱ አገራት በነሀሴ 2022 የተፈራረሙትን የ25 ዓመት የሃይል ሽያጭ ስምምነት ድጋሚ ማየት ሳይኖርባቸዉ አይቀርም ብሏል፡፡

እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ለኬንያ ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ አልሰጠችም ያለዉ ባለስልጣኑ፤ በኮንትራቱ መሰረት ደግሞ የተባለዉን የሃይል መጠን የማቅረብ ግዴታ ስላለባትም እስካሁን ምንም ያለችዉ ነገር የለም፤ነገርግን እኛ በሃይል አቅርቦት ደህንነቱ ላይ ስጋት አለን ሲል ገልጿል፡፡

‹‹ከሃይል አቅርቦት ደህንነት አንጻር ብንመለከተዉ ስጋት አለ፤ ኢትዮጵያ በኮንትራቱ መቋረጥ ለሚደርሰዉ ጉዳት ብትከፍል እንኳን አንድ መታወቅ ያለበት ነገር የሃይል ዉስንነት መኖሩን ነዉ፡፡ለዚህ ደግሞ ድጋሚ መስማማት አለብን››ሲሉ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዳንዔል ኪፕቶ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ያጋጠመ ችግር ባይኖርም ግን አሁንም ስጋት አለን ሲሉም አክለዋል፡፡

ኬንያ ከኢትዮጵያ በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት አንድ ኪሎዋት ሃይል በ6.5 የአሜሪካ ሳንቲም ለመግዛት መስማማቷ ይታወሳል፡፡ ሁለቱ አገራት በሃይል ሽያጩ ጉዳይ ድጋሚ ለመነጋገር የግድ አምስት ዓመታትን መጠበቅ አለባቸዉ፡፡በስምምነታቸዉ መሰረት ደግሞ ይህ የሚሆነዉ በፈረንጆቹ 2027 ነዉ፡፡

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችዉ ስምምነት 18 በመቶዉ በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል ለሚገኝ ከ8መቶ70ሺህ እስከ 1.4 ሚሊየን ለሚሆን የኬንያ አባወራ አስተማማኝ እና አቅምን ያገናዘበ የሃይል አቅርቦት ማድረስ እንድትችል ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ እያጋጠመ ያለዉ ከፍተኛ የሃይል እጥረት በገጠሪቱ ያሉ ኬንያዉያን ለከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ እና የሃይል አቅርቦት ዕጥረት እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል ነዉ የተባለዉ፡፡

የዓለም ባንክ በሚያዚያ 3 ባወጣዉ መግለጫዉ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ዜጎቿ እስካሁን ድረስ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የማያገኙባት አገር ናት ሲል ኢትዮጵያን በሰብ-ሰሃራን አፍሪካ ከሚገኙ ከፍተኛ የሃይል ዕጥረት ከሚያጋጥማቸዉ አገራት መካከል 3ተኛዉን ደረጃ እንደያዘች ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ለኬንያ ሃይል ከሚያቀርቡ ሁለት አገራት አንዷ ስትሆን ሌላኛዋ ኡጋንዳ ናት ዘ ኢስት አፍሪካን እንደዘገበው ፡፡

እስከዳር ግርማ

ሚያዝያ 07 ቀን 2016

Source: Link to the Post

Leave a Reply