የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በአማራ ክልል ንጹሃን ዜጎችን መግደላቸዉን ሂዩማን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት ገለጸ፡፡የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በአማራ ክልል መርአዊ ከተማ በጥር እና የካቲት ወ…

የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በአማራ ክልል ንጹሃን ዜጎችን መግደላቸዉን ሂዩማን ራይትስ ዎች ባወጣው ሪፖርት ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በአማራ ክልል መርአዊ ከተማ በጥር እና የካቲት ወራት ላይ ብዙ ንጹሃን ዜጎችን መግደላቸዉን ሂዩማን ራይትስ ዎች ባወጣዉ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡

በአማራ ክልል ከፋኖ ሚሊሻዎች ጋር በሚደረገዉ ጦርነት የፌደራሉ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች እጅግ ብዙ የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል ሲልም ነዉ የገለጸዉ፡፡

ተመድና የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ አዲስ ሰላም አስከባሪ ሃይል እንዳታሰማራ እንዲያግዱ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደግሞ በጉዳዩ ዙሪያ ገለልተኛ አጣሪ አካል እንዲመድብም ጠይቋል፡፡

ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከደረሱ ጉዳቶች ሁሉ ይህ የከፋዉ ነዉ ሲል የገለጸዉ ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ የፌደራሉ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሌሎች የጦር ወንጀሎችንም ስለመፈጸማቸዉ ማስረጃዉ አለኝ ብሏል፡፡

የፌደራሉ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች እያደረሱት ያለዉ አረመኔያዊ ግድያ መንግስት በክልሉ ሰላም እና ደህንነት ለማምጣት ነዉ እየሰራሁ የምገኘዉ ማለቱን በጽኑ የሚቃረን ነዉ ብሎታል፡፡

በክልሉ ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም ንጹሃን ዜጎች ለሞት እና ለከፋ ጉዳት እየተዳረጉ ነዉ ሲል ገልጿል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች በመርአዊ ምን ያህል ንጹሃን ዜጎች እንደተገደሉ ማረጋገጥ ባይችልም፤ የማህበረሰቡ መሪዎች ባቀረቡለት ዝርዝር ግን የ40 ሰዎች ስሞችን መመልከቱን አስታዉቋል፡፡

በሌላ በኩል ሶስት ነዋሪዎች ነገሩኝ ብሎ ይፋ እንዳደረገዉ ደግሞ ወደ 80 የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸዉን እና ግማሾቹ ሌላ ቦታ መቀበራቸዉን ነግረዉኛል ብሏል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች በቪዲዮ ተመልክቼዋለሁ ባለዉ መረጃ ደግሞ በፈረንጆቹ ጥር 30 ፤በመርአዊ ከተማ ዋና መንገድ ላይ 22 አስከሬን መመልከቱን እና ማህበረሱም አስከሬኑን እንዳይሰበስብ የፌደራሉ የጸጥታ ሃይሎች ሲከላከሉ መመልከቱን ስለማረጋገጡ ገልጿል፡፡

መንግስታዊ ያልሆነዉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ካዉንስል በመርአዊ 89 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸዉን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ ባደረገዉ መረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች 45 ንጹሃን ዜጎችን ገድለዋል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በፌደራሉ እና በክልል የጸጥታ ሃይሎች ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ሃላፊነት መዉሰድ አለመቻሉ ማባሪያ የሌለዉ ሞት እና ግጭት በአገሪቱ ላይ እንዲስፋፋ አድርጎታል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አጋር የሆኑት የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ የጦር ኮማንደሮች ህዝቡ ላይ ሲያደርሱ የነበረዉን ጭካኔ እንዲያቆሙ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስዱ እጠይቃለሁ ብሏል፡፡

እስከዳር ግርማ

መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply