የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በክረምት ወቅት ከመላው ሀገሪቱ 120 ሺ ዮኒት ደም ለመሰብሰብ እቅድ ይዣለው አለ፡፡አሁን እየተገባደደ ያለውን ሰኔ ወርን ጨምሮ እስከ መስከረ…

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በክረምት ወቅት ከመላው ሀገሪቱ 120 ሺ ዮኒት ደም ለመሰብሰብ እቅድ ይዣለው አለ፡፡

አሁን እየተገባደደ ያለውን ሰኔ ወርን ጨምሮ እስከ መስከረም 30 ፤በአዲስ አበባ ከተማ 40 ሺ ዮኒት ደም እና በመላዉ ሀገሪቱ ደግሞ በክረምቱ መርሀ ግብር 120ሺ ዮኒት ደም ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን አስታውቋል ።

የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት በክረምት የበጎ ፍቃድ ስራዎች በብዛት የሚሰራበት ወቅት ስለሆነ የደም ልገሳም አንዱ የበጎ ፍቃድ ስራ አካል እንዲሆን ሰፊ ጥረቶች እየተደረገ ነው ብለዋል።

ባሳለፍነው ግንቦት ወር በቀን 350 እና ከዛ በላይ ዩኒት ደም ሲሰበሰብ የቆየ ቢሆንም ሰኔ ወር ላይ ግን በቀን 200-250 ዮኒት ደም እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ተናግረው፤ ይህም ከባለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር መቀነሶች እንደሚያሳዩ ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን ወደ 50 የሚጠጉ ደም ባንኮች እንዳሉ እና ከነዛም መካከል በአማራ ክልል ወደ 10፣ በኦሮሚያ ክልል አዳዲስ የተጀመሩትን ጨምሮ ወደ 12 መኖራቸውን ጠቅሰዋል ።

የክልሎቹ እንቅስቃሴ ሲታይም ከፀጥታው ሁኔታ ጋር እና አጠቃላይ ካለው የበጀት አቅም ጋር ተያይዞ አፈፃፀማቸው ቋሚ አለመሆኑን አንስተው፤የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ያሉ የተወሰኑ የደም ባንኮች ተንቀሳቅሰው ለመስራት የሚቸገሩበት ሁኔታ መኖሩን ነግረውናል።

በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ድንኳኖችን ዋና ዋና አደባባዮች ላይ በመትከል ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር በጋራ በመሆን ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ደም የማሰባሰብ ስራዎች እንሚሰሩ ገልፀዋል ።

የተያዘው እቅድ እንዲሳካ ማህበረሰቡ ደም መለገስ መቀጠል እንዳለበት እና በክረምት ወቅት ደግሞ ታካሚዎች የሚበዙበት ሁኔታዎች ስለሚፈጠሩ በተለይ እንደ ወባ ያሉ በሽታዎች በየአካባቢው በስፋት የሚስተዋልበት ሁኔታ ስላለ እሱን ታሳቢ በማድረግ በክረምቱ የደም ልገሳው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በ 2016፤ 11 ወር ውስጥ አጠቃላይ ከነበሩ ደም ለጋሾች ወደ 3 መቶ 12 ሺ ዮኒት ደም ማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን ከዛም ውስጥ 38 % ድርሻውን ሴቶች ሲይዙ የቀረውን 62 % ደግሞ ወንዶች እንደሚይዙት ተናግረዋል።

ደም የሚለግሱ ሰዎች ያለምንም ችግር ደም ከለገሱ በኋላ መሄድ ይችላሉ ፣ ደሙን ለሚያገኘው ሰው ግን ህይወትን የማስቀጠል ጉዳይ ስለሆነ ማህበረሰቡ እሱን ታሳቢ አድርጎ ደም መለገስ ላይ በሰፊው እንዲሳተፍ የሚል ምልእክታቸውን አቶ ሀብታሙ አስተላልፈዋል።

በሐመረ ፍሬው

ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply