You are currently viewing የኢትዮጵያ ፖለቲካኞች ከናይጀሪያ ሕዝብ የሚማሩት አስኳል ጉዳይ አለ –ጎሰኛነትን መቅረፍ ይባላል—  አክሎግ ቢራራ (ዶር)

የኢትዮጵያ ፖለቲካኞች ከናይጀሪያ ሕዝብ የሚማሩት አስኳል ጉዳይ አለ –ጎሰኛነትን መቅረፍ ይባላል— አክሎግ ቢራራ (ዶር)

 

ኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ያላት መሆኗን የሚክድ ሁሉ ኢትዮጵያን እየካዳትና እየናዳት ነው። ይህች አገር ለመላው የጥቁር ዓለም ሕዝብ የነጻነት ተምሳሌት መሆኗንም መካድ ያመጣቸውን መዘዞች እስካሁን ለማጤንና አስተሳሰብን ለመቀየር አለመቻል ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚስክትለውን አደጋ ለማየት ይቻላል።

ኢትዮጵያ ከጎሳ ፖለቲካ ነጻ ሆና ወይንም ተላቃ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገር፤ ያለ ምንም ስጋት፤ የመኖር፤ ልጆቹን የማሳደግ፤ የግል ኃብት በራሱ ጥረትና ድካም የማግኘት፤ የመምረጥና የመመረጥ ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብቱ ሕጋዊ መብት ስኬታማ እስካልሆነባት ድረስ የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነትና ነጻነት ከድጡ ወደ ማጡ መሸጋገሩ አይቀርም። ዜጎቿ በምንም በኢትዮጵያዊነታቸው አንድነት ሊፈጥሩ የሚችሉበት ሁኔታ አይታይም። እርግጥ ነው፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል፤ በመላው ሕዝብ ድጋፍ ህወሓትን ለማፈራረስ ችሏል። ሆኖም፤ የጎሳው ፖለቲካ ስርዓት የሚያሳየው፤ ህወሓት ፈርሶ ሌሎች የህወሓት መሰሎች (Mirror images of the TPLF) ተረኛ ነን በሚል ሰበብ ተተኪነታቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ። ቤኒሻንግልና ኦሮምያ ምሳሌዎች ናቸው።

የዚህንን አደጋ ውጤት አስቀድሞ ለማየት መድፈር፤ መቻልና የጎሳውንና የቋንቋውን ስርዓት በባለሞያዎች አስጠንቶ (ነጻ ብሄራዊ ኮሚሽን) መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወያይበትንና የሚያጸድቀውን አማራጭ ማቅረብ ለኢትዮጵያ ዘላቂነትና ለመላው ዜጎቿ ደህንነት፤ ብልጽግናና ክብር ወሳኝ ሂደት ሆኗል።

የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር ሕዝቧ አይደለም። አገሪቱም አይደለችም። ችግሩ የዘውግ የፖሊቲካ ልሂቃንና ምሁራን ስግብግብነት፤ የእኔ ተራ ነው ባይነት፤ ሌባነትና ሙሰኛነት፤ የመሬት ተስፋፊነት ተደማምረው የሚካሄደው ያልተፈታ ስርዓት ወለድ የፖሊሲናን መዋቅራዊ ተግዳሮት ነው። ይህ ሁኔታ የሚረዳው እንደ ግብጽ ያሉትን ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ የሚመኙትን የውጭ ኃይሎች ጭምር ነው። ሱዳን እንዴት ደፍራ ኢትዮጵያን ወረረች? ብለን እንጠይቅ።

ወንድም በወንድሙ ላይ እልቂት ሲፈጽም “ይበለው” እያልን ውይንም ቸል ብለን እያየን የኢትዮጵያን ድሃ ሕዝብ ካለበት አሰቃቂ የኑሮ ደረጃ ነጻ ልናወጣው አንችልም።

እትዮጵያ ግዙፍ ለም መሬት ያላት መሆኑም በመረጃ የተደገፈ ሃቅ ነው። የዚህ መሰረት ደግሞ አገራችን የውሃና የወንዞች ማማ መሆኗ ነው። የዐባይ ወንዝ ለናይል ወንዝ 86 በመቶ የሚሆነውን የውሃ ድርሻ ያበረክታል። ስለዚህ፤ የናይል ወንዝ ያለ አባይ ወንዝ መጋቢነት ህልውና ሊኖረው አይችልም። ግብጽና ሱዳን ይህንን የተፈጥሮ ኃብት ሚና ወሳኝነት አብክረው ያውቁታል። ግብጾች የሕዳሴ ግድብ ስኬት ለግብጽ “ብሄራዊ ህልውና አስጊ ነው” ብለው ከፍተኛ ሁለገብ ጫናና የውክልና ጦርነቶች ያካሂዳሉ። ከዘዴዎቻቸው መካክል ሁለቱን እጠቅሳለሁ።

አንዱ ሱዳን ኢትዮጵያን እንድትወር ማድረግ ነው። ሁለተኛው ዘዴ የተዎካዮችን ጦርነት ማደራጀት፤ አቅማቸውን ማጠናከር፤ መሳሪያና መረጃዎች መለገስ ነው። ለዚህ አመች ሁኔታዎችን የፈጠረው በዘውግና በቋንቋ የተዋቀረው ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር ነው። ግብፅ ኢትዮጵያን በቀጥታ ለመውጋት የምትችልበት አቅም የላትም። ምክራ ተሸንፋለች። ግን፤ ግንባሮችን እየተንከባከበችና እየፈጠረች የምታደርገው የውክልና ጦርነት በቀላሉ አያቆምም። እኔ ትኩረት እንዲደረግበት በተደጋጋሚ የማሳስበው ከዚህ የውስጥ የተንኮኖል አደጋ ላይ ነው። ችግራችን የውስጥ ነው።

ይህ አደጋ ህወሓት ከስሟል ከሚለው ባሻገር እንዲታይ አሳስባለሁ። የግብፅ አሽከሮችና ተላላኪዎች በየቦታው እንደሚሰሩ ማመን ያስፈልጋል። የህወሓት ደጋፊዎችና ትርፍራፊዎች በካይሮና በካርቱም እንደ ገና እየተደራጁ ነው። ተልኳቸው ኢትዮጵያን ከማዳከምና ቢቻል ከማፈራረሱ ላይ መሆኑን አስመርበታለሁ።

የዚህ ሃተታ ፍሬ ነገር፤ ይህች መነሻዋን የምታውቅ ኢትዮጵያ ተብላ የምትታወቅ አገር ከሌሎቹ የጥቁር አፍሪካ አገሮች የተለየ፤ በዘውግና በቋንቋ የተዋቀረ፤ ለእርስ በእርስ ግጭት፤ ለእልቂት፤ ላለ መረጋጋት፤ ለውጭ ጠላቶች መግቢያ ወንፊቶችን ያመቻቸ የፖለቲካ ስርዓት የምትከተለው ለምንድ ነው? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳትና ከናይጀሪያ ሕዝብ የምንማረው አስኳል ልምድ መኖሩን ለማሳየት ነው። ይህ ስርዓት፤ በሰከነ አእምሮ፤ በጥናትና በምርምር በተደገፈና የሕዝቡን ድምፅና ፍላጎት በሚያንጸባርቅ ሕገ መንግሥትና ዘመናዊ አስተዳደር እንዲተካ አሳስባለሁ።

ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ ብዙ አገሮችና መንግሥታት አሉ። ናይጀሪያን መርጫለሁ።

ኢትዮጵያና ናይጀሪያ በመላው አፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሲነጻጸሩ አንደኛና ሁለተኛውን ደረጃ ይዘዋል። የናይጀሪያ ሕዝብ ቁጥር በ December, 29, 2020, 209 ሚሊየን ደርሷል፤ ከዓለም ሕዝብ 1.64 በመቶ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 116 ሚሊየን ሲሆን ከዓለም ሕዝብ 1.47 በመቶ መሆኑ ይነገራል። እነዚህ ሁለት አገሮች በመላው አፍሪካ የሚጫወቱት ሚና እያደገ ይሄዳል የሚሉ ታዛቢዎች አሉ። ናይጀሪያ ኃብታም እየሆነች ነው።

ሁለቱ አገሮች በጣም የተለያዩ ማህበረሰቦች እየመሰረቱ ነው። ለምንና እንዴት?

የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረችው ናይጀሪያ ነጻነቷን ከተጎናጸፈች በኋላ የገጠማት ዋና ተግዳሮት እንግሊዞች ትተውባት የሄዱት ወይንም ያወረሷት የፖለቲካና የአስተዳደር አወቃቀር ነበር። አንዱን ዘውግ ከሌላው ዘውግ፤ አንዱን ኃይማኖት ከሌላው ጋር የሚያናክስና የሚያጋጭ። የቅኝ ገዢዎች ደዌ፤ እርስ በእርሳችን እንድንጨራረስ ማድረጋቸው ነው።

ናይጀሪያ የተፈጥሮ ኃብት ባሌቤት ብትሆንም ቅሉ፤ ሰላምና እርጋታ የሌለባት አገር ነበረች። የፔትሮሊየም ኃብቷ ለተራው ዜጋ የገቢ መሻሻልን፤ የስራ እድልን ወዘተ አልፈጠረም ነበር። ከጅምሩ ተከታታይ የመንግሥት መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው በሙስና የተበከሉ፤ ለሕዝባቸው ምንም ደንታ የሌላቸው መሆኑ ይነግርላቸው ነበር። አንድ ጊዜ ለዓለም ባንክ ሌጎስን ስጎበኝ፤ አንድ ህንጻ ወድሞ አየሁና ታክሲ ነጅውን “ለምን ፈረሰ?” አልኩት። “በሙስና የተጠረጥሩት ፍተሻ ሲደረግ መረጃዎቹን ለመደበቅ ሲሉ ህንጻውን ቦምብ አደረጉት” ያለኝ እስካሁን አይረሳኝም።

ከሁሉም በላይ ግን ለናይጀሪያ ዋና የመናድና የመፈራረስ አደጋ ያስከተለው የዘውግ ልዩነት ነበር። ከJuly 6, 1967 እስከ January 15, 1970 የተካሄደው የቢያፍራ ጦርነት በዝቅተኛ ሲገመት አንድ ሚሊየን ንጹህ ዜጎች እንዲቀጸፉ ግብአት አድርጓል። በብዙ ሚሊየን የሚገመቱ ናይጀራዊያን ተፋልሰዋል፤ ተሰደዋል። ብዙ ቢሊየን ዶላር መዋእለ ንዋይ ኢንቬስትመንት ወድሟል። በዚህ የቀውጢ ወቅት የናጀሪያን መአከላዊ መንግሥት የመሩት ጀኔራል ያኩቡ ጎዎን (Yakubu Gowon) ነበሩ። የቢያፍራን ተገንጣይ እንቅስቃሴ የመሩት ደግሞ ኮሎኔል ኦጁኩ (Ojukwu) ነበሩ።

ጀኔራሉ ከሰሜን ናይጀሪያ ቢሆኑም መለያቸው ወታደራዊ ባለሞያና አገር ወዳድ መሆናቸው ነው። ፉላኒ ወይንም ሃውሳ ወይንም የእስልምና ወይንም የክርስትና ኃይማኖት ተከታይ መሆናቸው አልነበረም። ለናይጀሪያ የማይናጋ ብሄራዊ አንድነት ምስረታ ጉዞ የረዳት ይህ አገር ወዳድነትና የአብዛኛው የናይጀሪያ ሕዝብ ብሄራዊ አንድነት መሆኑን የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ግን፤ ኮሎኔሉ የታገሉት የኢቦ ዘውግ “ተገንጥሎ” ራሱን መቻል አለበት። “የተማረ ነው፤ ኃብት አለው” ወዘተ የሚሉ መለያዎችን ይከተሉ ነበር። ልክ ዛሬ የህወሓትና የኦነግ ሸኔ አጋፋሪዎች እንደሚያሰተጋቡት ሁሉ፤ በዚያ ወቅት የቢያፍራ ታጋዮች ብዙ ደጋፊዎች ነበሯቸው። በዓለም ደረጃም ተደማጭነት አግኝተው ነበር። የሃሰት ትርክት የተቀነባበረና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያስተጋቡት ከሆነ አገርን የሚያጠፋ ሁኔታ እንደሚፈጥር ከቢያፍራው ጦርነት ለመማር ይቻላል። ምእራባዊያን “እነዚህ እንስሳዎች እርስ በእርሳቸው ይጨፋጨፋሉ” እያሉ ይተቹ ነበር።

ካለፈው ታሪክ ለመማር የማይችሉ ስህተቱን በራሳቸው ላይ ይደግሙታል።  

የቢያፍራ ተገንጣዮች ብዙ የተማሩ ግለሰቦች እንደ ነበሯቸው አስታውሳለሁ። ግን፤ ተምረውም ቢሆን እንግሊዞች ስለ አውሮፓውያን የእርስ በእርስ እልቂት ታሪክ ሂደት ያስተማሯቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሞከሩ አይመስለኝም። ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ የሚሳለቁት አንዳንድ የአውሮፓ መሪዎችና መንግሥታት የአውሮፓ አገሮች በጦርነትና በእልቂት የታወቁ መሆናቸውን ጭምር ማወቅ ይኖርባቸዋል::

ታላቁ አገር ወዳድ መሪ ኦቶ ቦን ቢስማርክ (Otto Bon Bismarck) የተበታተኑትን የጀርመን ነገዶች በመሰብሰብ አንድ ታላቅና ዘመናዊ የሆነ የጀርመን አገር ከመመስረታቸው ከቨርሳይል ውል (The Treaty of Versailles፤ 1871) በፊት በፈረንሳዮችና በጀርመኖች መካከል የተካሄደው ጦርነት ለብዙ ሽህዎች ንጹህ ዜጎች እልቂት መሰረትና መነሻ ሆኖ ነበር። እነዚህ ሁለት ለአውሮፓ አገሮች መሰረት የሆኑ ሕዝቦች አንድ የተስማሙበት መጠቀስ ያለበት እሴት አለ።

ይኼውም፤ በጦርነት የሞተ ማንኛውም ግለሰብ በክብር መቀበር አለበት የሚለው ነው። The belligerent European nations agreed to guarantee every fallen soldier “the dignity and honor of a permanent and protected war grave.” ህወሓቶች የራሳቸውን መሪዎችና ታጋዮች ሲሞቱ መሞታቸውን ለመደበቅ በሚል እንስሳዊ አስተሳሰብ “አንገታቸውን ቆረጡ” የሚለውን ስሰማ፤ ታዲያ እነዚህ ለራሳቸው የዘውግ አባል ክብር የማይሰጡ እንዴት የሌላውን ሕይወት ለማክበር ይችላሉ? ወደሚል ትዝብት ተሸጋገርኩ። ማይካድራ ያደረጉትን ጭፍጨፋ አስታወስኩ።

የዚህ ፋይዳ ምንድን ነው?

በአውሮፓዊያን መካከል የተካሄዱት ተከታታይ ጦርነቶች ሁሉ አሰቃቂ እልቂቶች ያስከተሉ መሆናቸውን መርሳት የለብንም ለማለት ነው። የቢያፍራ ተገንጣዮች ከዚህ የእልቂት ታሪክ ቢማሩ ኖሮ ከአንድ ሚሊየን በላይ መስዋእት የሆኑትን ወገኖቻቸውን ይታደጓቸው ነበር።

በተመሳሳይ፤ የቢያፍራ ጦርነት ካለፈ ከአምሳ ዓመታት በኋላ የህወሓትና የኦነግ ሸኔ መሪዎች ከታሪክ አልተማሩም እንጅ ቢማሩ ኖሮ በተከታታይ ያካሄዷቸውና የሚያካሂዷቸው ዘውግና ኃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋዎች ለራሳቸውም ህልውና አስጊ መሆናቸው የማይቀር ነው። ለግብጾች አሽከር ሆኖ ጭፍጨፋ ማካሄድና አገርን መክዳት ከተጠያቂነትና ከሃላፊነት አያድናቸውም።

በጦርነት መሆኑ ባይካድም፤ በአውሮፓ የጅምላ ጭፍጨፋ ዘግናኝ ታሪክ ሂደት፤ ናዚዎች በአይሁዶች ላይ ካካሄዱት፤ የህወሓቱ ሳምሪ ቡድን በማይካድራ፤ ኦኖግ ሸኔ በሻሻመኔ፤ ሁለቱ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ነጻ አውጭ ግንባር ጋር ሆነው በመተከል ካካሄዱት ጋር ወዘተ ተመሳሳይነት አላቸው ። እልቂቱ ኢ-ሰብአዊ መሆኑን ማለቴ ነው። የታይምስ ጋዜጠኛ ሃዋርድ ራሰል (Howard Russel of the Times) በዚያ ወቅት በአካል ተገኝቶ የጻፈውን እንዳለ አቀርበዋለሁ። “No human eye ever rested on such revolting objects as were presented by the battle-fields—men’s bodies without heads, legs without bodies, heaps of human entrails (guts) attached to red and blue cloths, and disemboweled corpses in uniform.”

ይህ ለአይን የሚቀፍ ጭፍጨፋ በዛሬዋ ኢትዮጵያችን በማይካድራ፤ በመተከልና በሌሎች ቦታዎች በአውሮፓ ከዛሬ መቶ ሃምሳ ዓመት በፊት ከተካሄደው በባሰ ደረጃ ተካሂዷል። ወገኖቻችን በግሬደር መኪና እየተጫኑ በጅምላ በአንድ መቃብር ተቀብረዋል። የጎሰኛነትን ኢ-ሰብአዊነት ከዚህ ለመማር ይረዳል፤ ሰሚ ካለ።

የአውሮፓ መንግሥታት፤ በተለይ ፈረንሳይና ጀርመን እነዚህ ጭፍጨፋዎች እንዳይረሱና ተከታታይ ትውልድ እንዲማርባቸው በማሰብ ልዩ ልዩ ማስታወሻዎች ሰርተዋል (The French and Germans have constructed or allowed civil societies to construct memorials in these atrocity filed burial sites). እኛም ለተጨፈጨፉት ወገኖቻችን ሁሉ ማስታወሻዎችን እንዲሰሩ የማድረግ ወይንም የመስራት ግዴታ አለብን።

ለማጠቃለል፤ የቢያፍራ ተገንጣዮች ከታሪክ ባለ መማራቸው ከአንድ ሚሊየን በላይ ናይጀሪያዊያን ሞተዋል። ከጦርነቱ ወዲህ ግን የናይጀሪያ የፖለቲካ ልሂቃን በዘውግና በኃይማኖት የፖለቲካ ድርጅት መመስረት ለናይጀሪያ ብሄራዊና ግዛታዊ አንድነት፤ ታላቅነት፤ ልማት ማነቆ መሆኑን ተረድተዋል። ካለፈው ችግራቸው መማራቸው ያኮራል።

ናይጀራዊያን የፌደራል መንግሥት አላቸው። ግን መአከላዊው መንግሥት ጠንካራ እንዲሆን ብሄራዊ ስምምነት አለ። ቦኮ ሃራም ጥቃት ቢፈጽምም፤ አገሪቱን ሊበትናት አልቻለም። የዚህ መሰረቱ የናይጀሪያ ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዓላዊነት፤ ደህንነት እና በዜግነት ላይ የተመሰረተ የሕዝብ አንድነት ለድርድር አይቀርብም የሚል ራእይ ስኬታማ መሆኑ ነው። ናይጀሪያ 200 ዘውጎች ቢኖሯትም ወሳኙ መርህ ናይጀሪያና ናይጀሪያዊነት ሆኗል።  ከዚህ የምማረው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መሰረት መሆናቸውን ነው።

በአሁን ወቅት የናይጀሪያ ኢኮኖሚ ከአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ ከፍተኛውን ደረጃ ይዟል (GDP in excess of $400 billion፤ የደቡብ አፍሪካን ኢኮኖሚ ከበለጣት ቆይቷል።

በ2050 የናይጀሪያ ሕዝብ ቁጥር ከአሜሪካ ሕዝብ ቁጥር ይበልጣል።

ናይጀሪያ በፊልም ኢንዱስትሪ የአሜሪካን ሆሊውድ አልፋላች፤ ሕንድንም እንደዚሁ።

የናይጀሪያ ደራሲዎች በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነዋል።

የሌጎስ ከተማ 21 ሚሊየን ናይጀሪያኖች ይኖሩባታል። ኢቦ፤ ሃውሳ፤ ፉላኒ ወዘተ የሚሉት የጎሳ መለያዎች ወሳኝ ሚና መጫዎታቸው በዚህ በሌጎስ ከተማ አይታይም። “ልዩ ጥቅም ይገባኛል” የሚል ሰው አይሰማም። የሌጎስን ከተማ ለማሻሻልና ዘመናዊ ለማዳረግ የሚታየው ጥረትና ትኩረት ያኮራል። ከዚህ ለመማር የምንችለው ሌላ ክስተት አለ። ይኼውም፤ ከተሜነትና ዘውጋዊነት አብረው የማይሄዱ መሆናቸውን ነው።

ናይጀሪያዊያን ከራሳቸው ስህተት ለመማርና ከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ ለማካሄድ ከቻሉ እኛ ከእነሱ ለመማር ለምን አንችልም? የሚለውን ጥያቄ መልሻለሁ።

 

January 3, 2021

 

 

 

 

Leave a Reply