የኢትዮ ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በቀጣዮቹ ኹለት ሳምንታት ሥራ ይጀምራል

ህብረተሰቡ ከኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ንክኪ እንዲርቅ ተጠይቋል

አርብ ጥቅምት 11 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮ ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ኃይል ማስተላለፍ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
የኃይል ማስተላለፍ ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኮንስትራክሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ክብሮም ካህሳይ የተመራ ቡድን ከወላይታ ዞን አስተዳዳሪና የመምሪያ ኃላፊዎች ጋር እንዲሁም ከጋሞ ዞን አመራሮች ጋር ተወያይቷል፡፡
በመሰረተ ልማት ሥርቆት፤ ወሰን ማስከበርና የግንዛቤ በማስጨበጫ ሥራዎች ላይ ባተኮረው ውይይትም፤ መስመሩ ለኹለቱ አገራት የኃይል ትስስር እና ለአገራችን ኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ክብሮም አስረድተዋል፡፡
በዞኑ የኃይል ተሸካሚ ማማ ብረቶች በተደጋጋሚ መሰረቃቸውና ለመስመሮች ደህንነትና ለኮሙዩኒኬሽን የተዘረጋው ኦፕቲካል ግራውንድ ፋይበር እና ፋይበር ኦፕቲክስ መገናኛ ሳጥኖች በዘራፊዎች መወሰዳቸውን የገለጹት ክብሮም፤ ሥርቆቱ በሚደጋገምባቸው አካባቢዎች እስከ 6 ሜትር ከፍታ ብረቶቹን የመበየድ ሥራ ቢሰራም ሥርቆቱ አሁንም አለመቆሙን ገልፀዋል፡፡
እጅ ከፍንጅ በሚያዙ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው የህግ እርምጃም ከሚደርሰው አገራዊ ጉዳት አንፃር ተመጣጣኝ አለመሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቶ መግባባት ላይ መደረሱን ተነግሯል።
በውይይቱ የወሰን ማስከበር ሥራን በተመለከተም በዞኑ 5 ቤቶች ካሳ ተከፍሏቸው ያልተነሱ መኖራቸው የተነሳ ሲሆን፤ የዞኑ አመራሮች ካሳ ለተከፈላቸው ቤቶች ምትክ ቦታ በማዘጋጀት በአስቸኳይ እንዲነሱ እንደሚደረግ ቃል በመግባት ቤቶቹ የሚገኙበት ወረዳ አስተዳዳሪ ውሳኔውን እንዲያስፈጽሙ መመሪያ እንደተሰጣቸው ተገልጿል፡፡
ህብረተሰቡም መስመሩ ኃይል ያልተለቀቀበት መስሎት በመዘናጋት ጉዳት እንዳይደርስበት በህዝብ መድረክ፣ በማህበራዊ ሚዲያ እና ለነዋሪዎች ተደራሽ በሆኑ ዋና ዋና ሚዲያዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንዲሰራ መግባባት ላይ መደረሱንም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና በፕሮጀክቱ ሥራ መጀመር ዙሪያ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተመሳሳይ ውይይት መደረጉንም ክብሮም ገልፀዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሚያልፍበት የቦረና ዞን እንስሳትን የሚጠብቁ የህብረተሰብ ክፍሎች ኢንሱሌተሮችን ለጨዋታ በሚል እየሰበሩ በመሆናቸው፤ ድርጊቱን ለማስተው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር እንዲሰራ መጠየቁም ተገልጿል።

The post የኢትዮ ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በቀጣዮቹ ኹለት ሳምንታት ሥራ ይጀምራል first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply