የኢንተርኔት ማህበረሰብ፤ በአፍሪካ የኢንተርኔት አገልግሎትን ለማስፋፋት እንደሚሰራ ገለፀ

 በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በአፍሪካ የኢንተርኔት አጠቃቀም 23 በመቶ ጨምሯል

             በአፍሪካ የኢንተርኔት አገልግሎትን ለማስፋፋት በትጋት እንደሚሰራ የኢንተርኔት ማህበረሰብ (ISOC) ገለፀ፡፡ ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ግንኙነት ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገቡ መሆኑንና በ2000 ዓ.ም ከአንድ በመቶ በታች የነበረው የተጠቃሚ መጠን አሁን ወደ 30 በመቶ ማደጉን አስታውቋል፡፡
ሰሞኑን በሩዋንዳ ኪጋሊ “ያልተገናኙትን ማገናኘት፡- ዘላቂ ልማትን ማስመዝገብ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደ የዓለም የቴክኖሎጂ ልማት ኮንፈረንስ ላይ በአፍሪካ የኢንተርኔት ማህበረሰብ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት በቀለ  ባደረጉት ንግግር፤ በአህጉሪቱ የኢንተርኔት ግንኙነት ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ መምጣቱን ጠቁመው፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ  ጀምሮ ዕድገቱ መጨመሩን ገልፀዋል፡፡ ከ2019 እስከ 2021 ባሉት ጊዜያት በአፍሪካ የኢንተርኔት አጠቃቀም በ23 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል።
ምንም እንኳን ይህ አስደናቂ ዕድገት በአህጉሪቱ ቢታይም፣ አሁንም አስተማማኝና ተመጣጣኝ የኢንተርኔት አገልግሎት የሌላቸው ከ840 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂውን በመጠቀም ባለፈው ዓመት  የጀመረው ለእያንዳንዱ ዜጋ ልማትና ዕድገትን የማስፈን ተግባር ለማራመድ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ስምምነት ሲሰሩ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡
ትብብሩ ኢትዮጵያ የዲጅታል አገልግሎቶችን እንድታጎለብት እንዲሁም እንደ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አገልግሎትና ቱሪዝም ያሉ ዘርፎችን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማራመድ  እንድትችል ያደርጋታል ተብሏል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply