‹‹የኢንዱስትሪ መንደር መጠንሰሻዋ ከተማ ትኩረት ትሻለች››

‹‹የኢንዱስትሪ መንደር መጠንሰሻዋ ከተማ ትኩረት ትሻለች››

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 30/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በ1334 ዓ.ም በአፄ ሰይፈያሬድ እንደተመሠረተች ይነገራል። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የበጌ ምድር ጠቅላይ ግዛት ሆናም አገልግላለች። በአፍሪካ የመጀመሪያው ዘመናዊ የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር የተመሠረተባት ቦታም ናት፤ የድሮዋ ጁራ የአሁኗ ደብረታቦር።

ታሪካዊቷና የዕድሜ ባለጸጋዋ መናገሻ ቀድማ ጥበብ እና ስልጣኔን ብትጀምርም ከዕድሜዋ ጋር ማስቀጠል ግን አልቻለችም። በተለይም ከተማዋ ባለፋት መንግሥታት ትኩረት በማጣቷ የዕድሜዋን ያህል ማደግ ተስኗት ቆይቷል። ይሁን እንጅ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በተለይም በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየባት ቢኾንም አሁንም ግን የሚገጥሟት መሰናክሎች ባሰበችው ልክ እንዳትራመድ አድርጓታል።

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ኢንዱስትሪ ዞን ልማት ቡድን መሪ ዋለ አለሙ እንዳሉት ከተማ አስተዳደሩ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማዘመን ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ሁለት የኢንዱስትሪ ዞኖች አዘጋጅቷል። በእነዚህ የኢንዱስትሪ መንደሮች 65 ፕሮጀክቶች ፈቃድ አግኝተው በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ውስጥ ዘጠኙ በማምረት ላይ የነበሩ ቢኾኑም ሁለቱ በግብዓት አቅርቦት ችግር ማምረት አቁመዋል። ሃያ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ማሽን ለማስገባት በዝግጅት ላይ የሚገኙ ናቸው። አስር ፕሮጀክቶች ደግሞ በመሬት ዝግጅት እና ቁሳቁስ ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት ላይ ይገኛሉ። የተሰጣቸውን ቦታ አጥረው የተቀመጡ አራት ፕሮጀክቶች ደግሞ የወሰዱትን መሬት ተነጥቀዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ወደፊት ማልማት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ከሦስተኛ ወገን ያልጸዳ 80 ሄክታር መሬት በኢንዱስትሪ መንደሮች በሳይት ፕላን እንዲካተት አድርጓል። ለዚህም መንግሥት ለአርሶ አደሮች ካሳ የሚከፍልበትን ወይንም ባለሃብቱ ከሊዝ ውል የሚታሰብ ካሳ ለአርሶ አደሮች የሚከፈልበት አሠራር መዘርጋቱን አቶ ዋለ ነግረውናል፡፡

የአገልግሎት ዘርፉም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ቡድን መሪው ገልጸዋል። በዚህም ባለኮኮብ ሆቴሎች ግንባታ ላይ ይገኛሉ። በሪል እስቴት ለመሠማራት ባለሃብቶች ጥያቄ አቅርበዋል። የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ የሥራ ዘርፍ፣ በአጸደ ህጻናት እና በታሸገ ውኃ ማምረት ለመሠማራትም ጥያቄዎች ቀርበዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ‹‹ቁጥር አንድ›› እየተባለ በሚጠራው የኢንዱስትሪ መንደር ከሦስተኛ ወገን የፀዳ መሬት በ2010 ዓ.ም ካርታ አዘጋጅቶ ለፓርኮች ኮርፖሬት ደብረታቦር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስረክቧል። ይሁን እንጅ በከተማ አስተዳደሩ የነበሩ አራት ቀበሌዎች ወደ ፋርጣ ወረዳ መመለሳቸውን ተከትሎ በ2011 በጀት ዓመት የወረዳው መሬት፣ አጠቃቀም እና አካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የይዞታ ማረጋገጫ አረንጓዴ ደብተር በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች በመሥጠቱ በኢንዱስትሪ ልማቱ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን አቶ ዋለ ጠቅሰዋል።

ማልማት የጀመሩ ባለሃብቶች ጭምር በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እንደሚገኙ ነው አቶ ዋለ ያነሱት። በቅድመ ግንባታ ላይ የሚገኙት ስድስት ባለሃብቶችም በዚህ ችግር ምክንያት ሥራ ማቆማቸውን አንስተዋል። ለአርሶ አደሮች ካሳ ተከፍሏቸው እንዲነሱ ወይም የተሰጠው አረንጓዴ ደብተር መክኖ ባለሃብቶች በነጻነት እንዲያለሙ ለከተማ አስተዳደሩ እና ለዞኑ በተደጋጋሚ ጥያቄው ቢቀርብም እስከ አሁን ድረስ ችግሩ እልባት አላገኘም። ሌሎች ደብተር የሌላቸው አርሶ አደሮችም ችግር እየፈጠሩ መሆኑን አቶ ዋለ ነግረውናል። ችግሩ ከተቋሙ አቅም በላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዘላቂ የመንገድ፣ የመብራት፣ የውኃ እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮችም ለኢንዱስትሪ መንደሮቹ እንቅፋት ሆነዋል። የክልሉ መንግሥት ለኢንዱስትሪ መንደሮቹ እና ለባለሀብቶች በተዘጋጀው 80 ሄክታር መሬት ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች የካሳ ግምት በመክፈል አካባቢውን ለልማት ምቹ እንዲደረግ፤ የመሰረተ ልማት ችግሮችንም እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀለምወርቅ ምህረቴ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በከተማ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች የቦታ ባለቤት መሆን አለባቸው በሚል ከተማ አስተዳደሩ ለልማት እያዋለው በሚገኘው መሬት ላይ የመሬት ማረጋገጫ ደብተር በመሠራቱ ለሥራው እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን አቶ ቀለምወርቅ ነግረውናል፡፡

መሬቱን የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በመስጠቱ በልማቱ ላይ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ራሱን የቻለ የሚከታተለው አካል ተቋቁሞ የማጣራት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግራዋል፡፡ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ የሚያቀርበውን መረጃ መሠረት በማድረግ ውሳኔ እንደሚሰጥም አስገንዝበዋል፡፡ ደብተር ያልተሰጣቸው ደግሞ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰዳቸው የፍርድ ቤት ውሳኔን ለመጠበቅ አስገድዷል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንዱስትሪ ዞን የአካባቢ እንክብካቤ ተወካይ ዳይሬክተር በላቸው አቤልነህ እንዳሉት በዚህ በጀት ዓመት ቢሮው ለከተሞች ለመሠረተ ልማት የሚውል 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለፕላን ኮሚሽን ጠይቆ ነበር። ይሁን እንጅ ከተጠየቀው ገንዘብ የተፈቀደው 102 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው። በዚህም የኃይል ችግር ላለባቸው እና ቅድሚያ ማግኘት ለሚገባቸው እንደ ነፋስ መወጫ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ከሚሴ፣ እንጅባራ፣ ደብረ ብርሃን እና ኮምቦልቻ ከተሞች ቅድሚያ መሠጠቱን ነግረውናል። በቀጣይ የተጠየቀውን ገንዘብ ክልሉ መመደብ ካልቻለ የከተሞችን የመሠረተ ልማት ችግር መፍታት እንደማይቻል አቶ ዋለ ገልጸዋል።

የበጀቱ ችግር ለደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ከተሞች መሠረተ ልማት ለማሟላት ችግር ሆኗል፤ ለአርሶ አደሮችም ካሳ ከፍሎ ነጻ መሬት ለባለሃብቱ ማስተላለፍ አልተቻለም ብለዋል፡፡

ቢሮው ካለበት የበጀት ችግር አኳያ ካሳ የመክፈል አቅም ስለሌለው ባለሃብቱ ከሊዝ ታሳቢ የሚሆን ካሳ ከፍሎ እንዲገባ በመፍትሄነት ተቀምጧል። አሰራሩም ከባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተሞክሮ የተወሰደ እንደሆነ ነው የጠቆሙት።

ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

The post ‹‹የኢንዱስትሪ መንደር መጠንሰሻዋ ከተማ ትኩረት ትሻለች›› first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.

Source: Link to the Post

Leave a Reply