የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር የነበሩት እና በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ለበርካታ አመታት በሃላፊነት ያገለገሉት አቶ በቀለ ሙለታ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ሌሊት ላይ ህይወታቸው አልፏል።
የህይወት ታሪካቸው እንደሚያሳየው አቶ በቀለ ሙለታ፣ ከአባታቸው አቶ ሙለታ ቶላ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ወርቄ ዓለሙ በ1963 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተወለዱ።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወሰን ሰገድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሊድስታር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ወስደዋል።
በስራ ህይወታቸውም ከየካቲት ወር 1986 ዓ.ም እስከ ጥር 2000 ዓ.ም ድረስ በኢህአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ይዘጋጁ በነበሩ የተለያዩ ህትመቶች ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ሰርተዋል።
ከየካቲት 1 ቀን 2000 ዓ.ም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2001 ዓ.ም ድረስ በዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የአማርኛ ዜና ፣ አርቲክልና መጽሔት ዋና አዘጋጅነት፤ ከሚያዚያ 1 ቀን 2001 እስከ ሰኔ 30/2002 ዓ.ም ድረስ የፕሮሞሽን ዋና ክፍል ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል።
ከሐምሌ 1 ቀን 2002 ዓ.ም እስከ ጥር 30 ቀን 2004 ዓ.ም የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች ዋና ክፍል ኃላፊ፤ ከየካቲት 1 ቀን 2004 እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2006 የጥናትና ህዝብ ግንኙነት ማስተባበበሪያ መምሪያ ስራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል።
ከየካቲት 1 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /የዜናና ፕሮግራም ፕሮዳክሽን ዳይሬክቶሬት/ ዳይሬክተር እንዲሁም ከታህሳስ 17 ቀን 2007 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው መርተዋል።
ከነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓም እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የፋና ብሮድካስቲንክ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ተቋሙን መርተዋል።
በመቀጠልም ከታህሳስ 07/2013 እስከ የካቲት 17/2015 ዓ.ም ድረስ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል።
አቶ በቀለ፣ ባለትዳርና የአንድ ወንድና ሶስት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።
(ኢዜአ እንዳጠናቀረው)
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም
Source: Link to the Post