የኤምሬትስ አየር መንገድ አዉሮፕላን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አዉሮፕላን ጋር ሊጋጭ ነበር መባሉን የኤምሬትስ አየር መንገድ አስተባብሏል፡፡

የሶማሊያ አየር ተቆጣጣሪዎች ያደረጉት እንደሆነ በተጠረጠረ ድርጊት አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን እና ሌላ የኤምሬትስ አየር መንገድ አውሮፕላን ባለፈው እሁድ ወደግጭት አምርተው በመጨረሻ በፓይለቶች ጥረት እንደተረፉ ተዘግቦ ነበር፡፡

ታዲያ ይህንን ጉዳይ የኤምሬትስ አየር መንገድ አስተባብሏል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተናፈሰ የሚገኘዉ የሁለቱ አየር መንገዶች አዉሮፕላኖች ወደ ግጭት አምርተዉ ነበር የሚለዉ ዜና ስህተት ነዉ ሲል አየር መንገዱ አስታዉቋል፡፡

‹‹በተባለዉ ቀን እና ሰዓት ሁለቱ አዉሮፕላኖች አይደለም እስከ ግጭት የሚያደርስ ጉዳይ ይቅርና ለደህንነታቸዉ ስጋት የሚሆን ምንም ዓይነት መቀራረብ እንኳን እንዳልነበራቸዉ የኤምሬትስ አየር መንገድ ማረጋገጫ ማቅረብ ይችላል›› ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የኤምሬትስ አየርመንገድ አዉሮፕላኖች ደህንነቱ የተጠበቀ ጉዞ ማድረግ እና ርቀታቸዉን ጠብቀዉ መጓዝ የሚያስችላቸዉ መሳሪያዎችን የያዙ ናቸዉ ሲሉም አክለዋል፡፡

የሶማሊላንድ ሲቪል አቪዬሽን በቀድሞዉ ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ላይ ይፋ ባደረገዉ መረጃ መሰረት ቦይንግ 777 የተሰኘ የኤምሬትስ አየር መንገድ አዉሮፕላን ከኢትዮጵያዉ ቦይንግ 737 ማክስ አዉሮፕላን ጋር ለትንሽ ከመጋጨት መትረፉን አረጋግጫለሁ ሲል አስታዉቆ ነበር፡፡

ለዚህ ጉዳይም ተጠያቂ ያደረገዉ የሶማልያ አየር ተቆጣጣሪዎችን ሲሆን፤ የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ግን በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምንም የሰጠዉ ምላሽም ሆነ ማስተባበያ የለም፡፡

በተመሳሳይ በአንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በሌላ የኳታር አየር መንገድ አውሮፕላኖች ዙርያ ተመሳሳይ ድርጊት የዛሬ ወር ገደማ አጋጥሞ እንደነበር ይታወሳል።(ገልፍ ኒዉስ)

በእስከዳር ግርማ

መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply