የኤርትራ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካል አሉ ስትል ኤርትራ ከሰሰች

እሁድ ግንቦት 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ለረዥም ዓመት በጠላትነት ተፈራርጀው የቆዩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የጀመሩትን ግንኙነት ለማኮላሸት የሚጥሩ የውጭ ኃይሎች መኖራቸው ኤርትራ አስታውቃለች፡፡

የኤርትራ መረጃ ሚኒስቴር አርብ ግንቦት 4/2015 ባወጣው መግለጫ፤ “የ2018ቱ ታሪካዊው የኤርትራ እና የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ለመረበሽ እና ሂደቱን ለማደናቀፍ በተለይም የውጭ ኃይሎች የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም” ሲል ክሷል፡፡ ይሁን እንጅ የኹለቱን አገራት ግንኙነት ለማኮላሸት እየጣሩ ነው የተባሉ የውጭ ኃይሎች ማንነት በውል አልተገለጸም፡፡

አገራቱ በወቅቱ ያደረጉት የሰላም ስምምነት በውል የማይታወቅ ቢሆንም፤ ኹለቱም በኩል ግንኙነቱን ለማስቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይሰማሉ፡፡ ይሁን እንጅ በግንኙነቱ ላይ ጥያቄ የሚነሳ ሲሆን፣ የኹለቱ አገራት ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሰረ እና በግልጽ ስምምነት ወረቀት ላይ የሰፈረ አይደለም የሚል ተደጋጋሚ ትችት ይቀርብበታል፡፡

የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ተቋማዊነትና ዘላቂነት ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር ጥያቄ የነተሳበት ሲሆን፤ በምክር ቤት ደረጃ ጥያቄው ከተነሳ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ በወቅቱ የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ቀጣይነት ላይ ማብራሪያ ጠይቆ ነበር።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት ደመቀ መኮንን፤ በኢትዮጵያ በኩል ግንኙነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ “የተከፈተው የሰላም በር በሚፈለገው ልክና ሊኖረን ከሚገባው ትብብር አኳያ የሚፈለገውን ያህል አድጓል ብሎ መውሰድ አይቻልም” ማለታቸው አዲስ ማለዳ በወቅቱ መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡

በሌላ በኩል ኤርታራ ባወጣችው መግለጫ፤ ኹለቱ አገራት በሕወሓት ተከፍቷል ባሉት የሰሜኑ ጦርነት ያጋጠማቸውን ትልቅ ስጋት ለመመከት በጸረ-ማጥቃት ዘመቻው በትክክል መተባበራቸውን አምናለች። የኤርትራ ሰራዊት በሰሜኑ ጦርነት የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ውንጅላ ከሕወሓት እስከ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይቀርብበታል፡፡

The post የኤርትራ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካል አሉ ስትል ኤርትራ ከሰሰች first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply