
የእስራኤል ዲፕሎማት ከአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸው ተነገረ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 12 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የእስራኤል መንግስት አንጋፋ ዲፕሎማት እየተካሄደ ካለው ከአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸው ተገለፀ። አጋጣሚው የተከሰተው እስራኤል በህብረቱ ያላት ይፋዊ ተቀባይነት ከፍተኛ ውዝግብ ላይ በደረሰበት ሰአት መሆኑ ተነግሯል። በማህበራዊ ሚድያ መድረኮች በተዘዋወረ አንድ ቪድዮ የእስራኤል ዲፕሎማት የሆነችው አምባሳደር ሻሮን ባርሊ ትላንትና በተደረገው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ የደህንነት ጥበቃ አባላት ከጉባኤው አዳራሽ ሲያስወጧት ታይቷል። የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ቃለ አቀባይ የሆኑት ኤባ ካሎንዶ እንደተናገሩት ዲፕሎማቷ ከጉባኤው እንድትለቅ የተደረገችው በስብሰባው ለመሳተፍ አግባብ ያለው ፈቃድ የተሰጣቸውና እንዲሳተፉ የሚጠበቁት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ግለሰብ ባለመሆናቸው ነው። በተጨማሪም ሌላ የህብረቱ ባለስልጣን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለፁት በህብረቱ ጉባኤ እንዲሳተፉ ይፋዊ ፈቃድ የተሰጣቸው በአፍሪካ ህብረት የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት አለልኝ አድማሱ ሲሆኑ ይህ ፈቃድም ለሌላ ግለሰብ መተላለፍ የማይችል ነው። ድርጊቱን እስራኤል የኮነነችው ሲሆን የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጠው ምላሽ “በጉባኤው በታዛቢነት አግባብ ያለው ፈቃድና ባጅ ቢሰጣትም፣ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆነችው አምባሳደር ሻሮን ባርሊን ከስብሰባው ታዳሚነት በማስወጣት የፈፀመውን ድርጊት እስራኤል በአፀያፊነት ትመለከተዋለች” ብሏል። አዲስ ዘይቤ እንደዘገበው።
Source: Link to the Post