የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማህበር  ከኃይለማርያም እና ሮማን ፋዉንዴሽን  ጋር ተዋሀደ።በቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ አነሳሽነት በ2006 ዓ.ም የተቋቋመዉ እና በ…

የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማህበር ከኃይለማርያም እና ሮማን ፋዉንዴሽን ጋር ተዋሀደ።

በቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ አነሳሽነት በ2006 ዓ.ም የተቋቋመዉ እና በአዲስ አበባ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የህጻናት የቁርስና ምሳ ምገባ ፕሮግራም ፈር ቀዳጅ በመሆን ከ21 ሺህ በላይ ደሀ ህጻናትን ሲመግብ የነበረዉ የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማህበር ከኃይለማርያም እና ሮማን ፋዉንዴሽን ጋር መዋሀዱን ፋውንዴሽኑ ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማህበር ከበጎ አድራጊ ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦች እዲሁም የተለያዩ ተቋሞች የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ ሲያካሄደዉ የቆየዉ የምገባ ፕሮግራም ህጻናት በምግብ እጦት ምክንያት ለጤና እና ለስነልቦና ጉዳቶች እንዳይዳረጉ አንዲሁም ከትምህርት ገበታቸዉ እንዳይስተጓጎሉ በማድረግ ለትምህርት ተደራሽነት እና የኢኮኖሚ ጥራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ድርጅት ነዉ፡፡

በተጨማሪም የእናት ወግ በምገባ ስራዉ ላይ ለተሰማሩ ከ1 ሺህ 500 በላይ ችግረኛ ሴቶች የስራ እድል በመፍጠር የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር ሲሰራ ቆይቷል፡፡

የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማህበር መልካም ተሞክሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2012 ዓ.ም በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለጀመረዉ የምግባ ፕሮግራም እንደሞዴል ያገለገለና መሰረት የጣለ ዉጤታማ የበጎ አድራጎት ስራ ነዉ፡፡

የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማህበር ወደ ኃይለማርያም እና ሮማን ፋዉንዴሽን የተዋሃደዉ በድርጅቱ ሲከናወኑ የቆዩ የስርአተ ምግብና የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራዎችን በማጠናከር እና በዘላቂነት ለማስቀጠል እንዲቻል ነዉ፡፡

የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማህበር በዚህ ዘርፍ ያካበተዉ የበርካታ አመታት ተሞክሮ ኃይለማርያም እና ሮማን ፋዉንዴሽን በስርአተ ምግብና የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዙርያ ለሚያካሂዳቹ የአድቮኬሲ ስራዎችና ፕሮግራሞች ጠንካራ መሰረት የሚጥሉ ናቸዉ፡፡

በየውልሰው ገዝሙ
ሕዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply