“የእናንተ እረኝነት እየጨረሰን ካለው ክፉ አውሬ እንዲታደገን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን” ሲል የሞዐ ግብረ ኃይል ቅዱስ ሲኖዶስን ጠየቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 12 ቀን 201…

“የእናንተ እረኝነት እየጨረሰን ካለው ክፉ አውሬ እንዲታደገን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን” ሲል የሞዐ ግብረ ኃይል ቅዱስ ሲኖዶስን ጠየቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የሞዐ ግብረ ኃይል ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እና ጥፋት ለመከላከል ይቻል ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ዋና ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ምእመናንን ይታደግ ዘንድ ጠይቋል። ግብረ ኃይሉ ከምእመናን የቀረቡ አስቸኳይ ምላሽ የሚጠይቁ ጉዳይ ያላቸውን ነጥቦች ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቧል። ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንን ከጥቃት ለመታደግ የሚያስችሉ ነጥቦች ዙሪያ ውሳኔ እንዲሰጥ ፤ ምእመናን ወጥ አቋም እንዲይዙ ለተግባራዊነቱም በሙያቸው ሊያግዙ የሚችሉ ምእመናንን፣ ሙሁራንን ፣ ማኅበራትን ፣ ሰንበት ቤትን ያካተተ ግብረ ኃይል እንዲመሰረት እና በቅዱስ ሲኖዶስ የሚመራ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ፤ ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲቃወሙት እና እንዲያውቁት ማወጅ ፤ በቤተ ክርስቲያን ስም ምእመናንን የሚያዳክሙ ከፋፋዮችን ምእመናን እንዳይከተሏቸው በግልፅ ማወጅ እና መሰል ነጥቦችን ጠቁሟል። በተለያዩ ቋንቋዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ዘመቻ መንግስት በሕግ ተጠያቂ አለማድረጉን ይልቁኑም ተባባሪ በመሆን መቀጠሉን እና የእርምት እርምጃ ባለመውሰዱ ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ገልፆ ይልቁንም ለኦርቶዶክሳውያን የፍትህ አገልግሎት አለመስጠቱን ፤ መልሶም አለማቋቋሙን ፤ ለወደፊትም ዋስትና አለመስጠቱና በፓሊሲው ውስጥ አለማካተቱን የችግሩ ተባባሪ መሆኑን እንደሚያሳይ የሞዐ ተዋሕዶ ግብረ ኃይል ያደረሰን መረጃ ያመለክታል። ይህንንም ሁሉ የኦርቶዶክሳውያን ግፍ እና መከራ አለፍ ሲልም ሞት ለማስቀረት ቅዱስ ሲኖዶስ በአስቸኳይ ቢፈጽማቸው ይጠቅማሉ ያላቸውን 10 ነጥቦች ለቅዱስ ፖትርያርኩ እና ለብፁዓን አባቶች የሞዐ ግብረ ኃይል አቅርቧል። 1. መንግስት በሀሰት ትርክት ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶችን ፣ፖሊሲዎችን ፣ የኪነጥበብ ውጤቶችን በአዋጅ እንዲያግዳቸው ማድረግ 2. በተለይ ባለፉት 4 ዓመታት በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ኦርቶዶክሳውያንን ለጥቃት ያጋለጡ የፓለቲካ መዋቅር ፣ የፓለቲካ ማንፌስቶ ፣ ንግግሮች በሕግ አግባብ እንዲለወጡ ፤ ፈፃሚዎቻቸው እንዲጠየቁ እና ከስልጣናቸው ተነስተው እንዲከሰሱ፣ 3. ኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰውን ሁለ ገብ ጥቃት በመዘርዘር አጥፊዎች እንዲጠየቁ ፤ ጉዳት የደረሰባቸው ካሳ እንዲያገኙና መልሰው እንዲቋቋሙ ፤ዋስትናም የሚሰጥ ዕቅድ በመንግሥት እንዲቀርብ ። 4. ክርስቲያኖች ባሉበት ቦታ ሁሉ በሀገር ባለቤትነት ከሌሎች ጋር እኩል የሚሳተፉበት አሰራር እንዲዘረጋ ዝርዝር መንግስታዊ ውሳኔዎች የትግበራ ዕቅድ መጠየቅ፣ 5. ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት የፈጠሩትን የሀሰት ትርክቶች እና የፈጠራ ክሶች በዕውቀት እና በማስረጃ የሚሞግት የሕግ ፣ የነገረ መለኮት ፣ የፖለቲካ ምሁራን ግብረ ኃይል አቋቁሞ ምላሾችን ማዘጋጀት እና በትምህርት ማሰራጨት፣ 6. የቤተ ክርስቲያኒቱን ዘመናዊ እና የአብነት ትምህርት ቤት ሊቃውንት በጋራ የሚያዘጋጁት ትምህርቶች የምእመናንን አንድነት የማስመለስ ዘመቻ መጀመር፣ 7. በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸውን እና የተከበሩትን ልሂቃን በመጥራት የፖለቲካ ተሳትፏቸው ምን መምሰል እንዳለበት አባታዊና ክርስቲያናዊ ትምህርት እና ምክር መስጠት፣ 8. ከአኃት እና ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ከሌሎችም የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ጋር የጋራ ዓለም አቀፍ ዘመቻዎችን የሚያስተባብር ግብረ ኃይል አቋቁሞ በአስቸኳይ ወደ ስራ መግባት፣ 9. የሕግ ባለሙያዎችን ከማደራጀት ባለፈ የሕግ ጥሰት ሲኖር ተጠያቂነት እንዲኖር እና ለመጪውም ምእመናንን ከጥቃት መከላል የሚያስችል ሥራ መስራት፣ 10. ቤተክርስቲያን እና ልጆቿ ላይ የሚደርሰውን አካላዊ እና ስነ ልቦና ጥቃት ለመቀነስ ለሚመለከታቸው አካላት ማለትም ለመንግሥት ፣ለኦሪየንታል እና ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ፣ ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፣ ለተባበሩት መንግስታት ፣ ለአውሮፓ ሕብረት ፣ ለአፍሪካ ሕብረት ፣ ተሰሚነት ላላቸው የሠብአዊ መብት ተሟጋቾች ወዘተ…የእወቁልኝ ተገቢውን ጥሪ ማስተላለፍ ያስፈልጋል ብሏል። በሀገራችን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ችግሮችን ለመፍታት ሥራ መጀመሩን ያስታወሰው ግብረ ኃይሉ በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የቤተ ክርስቲያን መገለጫዎች ማለትም የሰንበታቱን ፣ የቀን እና የዘመን አቆጣጠር ፣ የአደባባይ በዓላት አከባበር ፣ የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ፣የግዕዝ ቁጥር እና ፊደላት ጉዳይ ወዘተ ለድርድር ለማቅረብ የሚሞክሩ አካላት እንዳሉ መረጃዎች እየወጡ እንደሆነ ጠቁሞ ከኮሚሽኑ ጋር የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን እንዲመካከሩበት ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን እና ምሁራን የተውጣጣ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ሞዐ ተዋሕዶ ቅዱስ ሲኖዶስን ጠይቋል ። በመጨረሻም “የእናንተ አባትነት እና እረኝነት እኛ ልጆቻችሁን እየጨረሰን ካለው ክፉ አውሬ እንዲታደገን ጥሪያችንን ሰምታችሁ እስከ መሥዋዕትነት በሚደርስ የአባትነት ፍቅር ትታደጉናላችሁ ብለን ተስፋ እናደርጋለን ” ብሏል። ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳጋራው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply