
“የኦህዴድ/ ብልፅግና መንግሥት ቀውስ እየጠመቀ ሀገር ማወኩን ያቁም!” ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ … ሀምሌ 19/2015 ዓ/ም_አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ:_ የነፃነት ቀንዲሏ እና የሶስት ሺ ዓመት ታሪክ ባለቤት የሆነችውን ሀገር ኢትዮጵያ በህወኃት የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ታሪኳ እየደበዘዘ መጥቷል፡፡ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ተገምደውና ተሰናስለው በኖሩበት ሀገር በዘር ፖለቲካ ያበዱ መሪዎች ሀገራችን የቆመችበትን ምሰሶ በሀሰት ትርክት እየናዱት ይገኛል፡፡ የኢህአዲግ/ህወኃት መራሹ መንግስት ከአምስት ዓመት በፊት በህዝብ ትግል ከተገረሰሰ በኃላ የተካው የኦህዴድ/ብልፅግና መንግስት መረጃን በማሳከር፡ በሃሰት ውንጀላ፡ እና ዜጎችን በመከፋፈል የተዋጣለት ሁኖ ቀጥሏል፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በርካታ ወገኖቻችን ለህልፈተ ህይወት እየተዳረጉ እንደሆን የየእለቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የወገኖቻችን የግፍ ግድያ፣ረሀብ፣ የፍትህ እጦት፣ ዘረኝነት የሀገሪቱ የእለት ክንውን ሁኖ ቀጥሏል፡፡ ዛሬም የሰቆቃ እና የድረሱልን ጥሪዎች በተለያዩ ክልሎች ይሰማሉ፡፡ በጋምቤላ ክልላዊ መንግስት በአኙዋክ እና በኑዌር መካከል የተፈጠረው እልቂት በ1994 ዓ.ም. በአኙዋክ ላይ የተፈጠረውን የዘር ማጥፋት ለመድገም የተጠነሰሰ የፖለቲካ ሴራ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በጉጅ አካባቢ የሚታየውም አመፅ እና የፍትህ እጦት፣ የጉራጌ እና የወላይታ ማህበረሰቦች ህገመንግስታዊ የሆነ የክልልነት መብታቸዉን ስለጠየቁ ብቻ ባላቋረጠ ሁኔታ እየደረሰባቸዉ ያለዉ በደል የስርዓቱን ቅጥ ያጣ ጭቆና የሚያሳዩ ተግባሮች ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎሳ ፖለቲካው አስፀያፊ ገፅታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተንሰራፍቶ ቦታ ከያዘ ውሎ አድሯል፡፡ ዓለማዊ ምቾትና ደስታን ተፀይፈው ለሰማያዊው መንግስት ራሳቸውን ያስገዙ መነኮሳት በብሄር ተቧድነው ሲነካከሱ ማየት እጅጉን ልብ ይሰብራል፡፡ ለሁሉም የሰው ልጆች ደህንነት መቆም ሲገባቸው ጎሳን ለይተው የሚያለቅሱ አባቶችን ማየት የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል፡፡ የኦህዴድ/ብልፅግና ስርዓት ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቅዱስ ሲኖዶሱ እውቅና ውጭ አዳዲስ ጳጳሳትን አይን ባወጣ መንገድ ለመሾም ያደረገው ጥረት በተወሰኑ በቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪዎች እና በምዕመኑ ተጋድሎ ለጊዜው ሊከሽፍ ችሎ ነበር፡፡ ይሁንና በቅርቡ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ሚኒስተር አብይ ጋር ባደረጉት መሞዳሞድ ድሉ ሊቀለበስ ችሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ በትግራይ ክልል የተከናወነውን ከቀኖና ያፈነገጠ አዳዲስ ጳጳሳትን የመሾም ድርጊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያ ከማዉገዝ አልፋ ምዕመኗን በማስተባበር በኦህዴድ/ብልጽገና መንግስት ላይ ተፅዕኖ ፈጥራ ልታከሽፈው ይገባል፡፡ በቤተ ክርስቲያንዋ ላይ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን እያደረገ ያለውን ስርዓት ከመማፀን ይልቅ ያላትን ህዝባዊ አቅም ተጠቅማ ስርዓቱ ላይ ተፅኖዋን ፈጥራ መብቷን መስከበር ይኖርባታል፡፡ ከላይ የተጠቀሱ እሳቤዎች ላይ በመንተራስ ባልደራስ የሚከተሉት ጉዳዬች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጥሪውን ያቀርባል። በቤኒሻንጉል ጉምዝ የኦህዴድ/ብልጽግና መንግስት በእጅ አዙር እያሰለጠነ እና እያስታጠቀ ከእነቡድን መሳሪያቸዉ ጫካ እንዲገቡ እና በአካባቢዉ በሚኖሩ አማሮች ላይ እንደለመዱት አስከፊ በማነነት ላይ የተመሰረተ ጭፍጨፋ እንዲፈጽሙ የምስደረጉን እቅድ ጠንሳሹ መንግስት በአስቸኳይ እንዲያስቆም እንጠይቃለን፣ ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ታጣቂዎች ከኦነግ ጋር በመናበብ በጋምቤላ ክልል በአኙዋክ እና በኑዌር ማህበረሰቦች ላይ እያደረሱ ያሉት ተደጋጋሚ ዘመቻ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ ይኸ ጥቃት የኦህዴድ/ኦነግ ጥምረት በጋምቤላ ውስጥ ለመስፋፋት የሚያደርገው ዘመቻ አካል መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በጋምቤላ ውስጥ በኢትዮጵያዊነታቸው በሚኮሩ በአኙዋክ እና በኑዌር ማህበረሰቦች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ፓርቲያችን እንዲቆም እየጠየቀ፣ የኦህዴድ/ኦነግ/ብልፅግና መንግሥት በዚህ በጋምቤላ ክልል እየደረሰ ካለው ጥቃት የክልሉን ማህበረሰቦች ሊታደጋቸው አለመቻሉን ፓርቲያችን በጽኑ ይቃወማል፡፡ ለተደጋጋሚ ጊዜያት በአንዩዋክ ማህበረሰብ አባላት ላይ ግድያ የፈጸሙ ወንጀለኞችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ፓርቲያችን ይጠይቃል። ሕገ መንግሥታዊ የሆነ የክልልነት ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ በጉራጌ እና በወላይታ ማህበረሰቦች ላይ እየደረሰ ያለው እስራት፣ እንግልት እና ግድያ እንዲቆም ፓርቲያችን ይጠይቃል፡፡ በጉጅ ዞን የዞን አደረጃጀትን አስታኮ የተፈጠረዉን ግጭት ያካባቢውን ህዝብ ጥያቄ ሊያስተናግድ የሚችል መልስ እንዲሰጠው እና የህዝቡ የፍትህ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ እንጠይቃለን፡፡ በአማራ ክልል የክልሉ ምክር ቤት ሳይጠየቅ የገባው የመከላከያ ኃይል በትጥቅ ትግል በማይሳተፉ ሲቪል ሰዎች ላይ እያደረሰ ያለው የግድያና የንብረት ጥፋት በመገናኛ ብዙሃን እየተዘገበ ይገኛል፡፡ በፋኖ ታጣቂ ኃይሎችና በመከላከያ መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ሳቢያ በክልሉ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ፣ የክልሉ ማህበረሰብ እየጠየቀ ባለው መሰረት፣ የመከላከያ ኃይሉ ወደዬጦር ሰፈሮቹ (ካምፖቹ) እንዲመለስና ግጭቱ ቆሞ በተፋላሚዎቹ መካከል የሰላም ድርድር እንዲጀመር ፓርቲያችን ይጠይቃል፡፡ ፖለቲካዊ ድርድርን በየወረዳው በሚደርግ ባህላዊ ሽምግልና ለመተካት መሞከር ድርድሩ ሀገራዊ ይዘት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ሳይሆን በአካባቢ ጉዳዮች ላይ እንዲጠመድ በማድረግ ወደ መሠረታዊ መፍትሄ የሚወስደውን መንገድ የሚዘጋ ከመሆን ሊዘል አይችልም፡፡ ይህ ዓይነት ሙከራ አዘናጊ ከመሆኑም በላይ የክልሉን ማህበረሰብ ለተጨማሪ ጥቃት የዝግጅት ጊዜ መግዣ በመሆን የሚያገለግል ነው፡፡ በመሆኑም ድርድሩ በአማራ ማህበረሰብ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ የሚፈታና ተያያዥ በሆኑ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ የሚያተኩር ሊሆን ይገባል ብሎ ፓርቲያችን ያምናል፡፡ በአማራ ክልል ማዳበሪያ በበቂ መጠን ሊቀርብ ባለመቻሉ ምክንያት በክልሉ የሚታረሰው የእርሻ መሬት ፆም ሊያድር ስለሆነ፣ በሚቀጥለው ዓመት በክልሉ የርሀብ አደጋ ሊያንዣብብ ይችላል፡፡ በመሆኑም የአማራ ገበሬዎች ያቀረቡት የማዳበሪያ ጥያቄ በአስቸኳይ የሚፈታበት ዘዴ እንዲገኝ ፓርቲያችን በአፅንኦት ይጠይቃል፡፡ በአፋርና በሱማሌ ክልሎች መካከል በየጊዜው በሚካሄደው ግጭት ምክንያት በሁለቱም ክልሎች ባሉ ኢትዮጵያዊያን አፋሮችና ሱማሌዎች ከባድ የህይወትና የንብረት ጥፋት እያስከተለ ነው፡፡ ይህ የመላው ኢትዮጵያ ጉዳት ስለሆነ፣ ግጭት ጠማቂ የሆነው የኦህዴድ ብልፅግና መንግሥት በእጅ አዙር የሚያራግቡ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የፌድራል መንግሥቱ ከዚህ ድርጊቱ ተቆጥቦ የሁለቱም ማህበረሰቦች አመራሮች ልዩነታቸውን በድርድር እንዲፈቱ ፓርቲያችን ይማፀናል፡፡ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሐምሌ 18/2015 አዲስ አበባ
Source: Link to the Post