“የኦሮሚያ ሲኖዶስ መንበረ ጴጥሮስን” መሠረትን ባሉ ግለሰቦች ላይ የ10 ቀን ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

“የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ጴጥሮስን መሥርተናል፤” በሚል፣ በሸገር ከተማ አስተዳደር፣ ባለፈው ማክሰኞ መግለጫ ሲሰጡ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች፣ ፍርድ ቤት ቀርበው የዐሥር ቀን ተጨማሪ የምርመራ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል።ፖሊስ፣ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ፣ በሸገር ከተማ አስተዳደር የናኖ መልካ የመጀመሪያ ፍርድ ደረጃ ቤት ባቀረባቸው ግለሰቦች ላይ፣ 14 ቀናትን ለምርመራ ጠይቆባቸው፣ ፍርድ ቤቱ 10 ቀን መፍቀዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. “የኦሮሚያ እና ብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” መሥርተናል ብለው በተደረገው ስምምነት ከተመለሱት 25 መነኮሳት ውስጥ አራቱ አባቶች፣ በአሁኑ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኙበት ታውቋል።“መንበረ ጴጥሮስን መሥርተናል” በማለት መግለጫ ከሰጡት ውስጥ ሦስቱ፣ በዚያው ዕለት ምሽት በመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ተይዘው የታሰሩ ሲሆን፣ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ኢ-ቀኖናዊ ድርጊት በፈጸሙት በእነዚኽ ግለሰቦች ላይ ክስ እንዲመሠረት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን በቃል እንደጠየቁ፣ የቅርብ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አወያይነት፣ በሕገ ወጥ መንገድ ኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት መነኮሳት፣ ከመሰል ድርጊቶች ለመታቀብ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋራ በተደረሰው ስምምነት፣ ውግዘቱ ተነሥቶላቸው ሥልጣነ ክህነታቸው እንደተመለሰላቸውና የሥራ ላይ መብታቸው እንደተጠበቀላቸው መገለጹ ይታወሳል።
ዓመቱን ጠብቀው፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና ውጪ እና ስምምነቱን በሚፃረር መልኩ እንደሰጡት በተነገረው መግለጫ ለእስር መደረጋቸው ለብዙዎች አነጋጋሪ ኾኗል።
ከእንቅስቃሴው ጋራ በተያያዘ፣ እስከ አሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉት መነኮሳት እና ሌሎች የ”መንበረ ጴጥሮስ ምሥረታ” አስተባባሪዎች ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ቁጥር ዘጠኝ እንደደረሰ ተመልክቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply