የኦሮሚያ ቤተ ክህነት በሚል የተቋቋመው ኮሚቴ ያነሳቸው ችግሮች በጠቅላይ ቤተ-ክህነት እንዲፈቱ ዕርቅ ፈጸመ

የኦሮሚያ ቤተ ክህነት በሚል የተቋቋመው ኮሚቴ ያነሳቸው ችግሮች በጠቅላይ ቤተ-ክህነት እንዲፈቱ ዕርቅ ፈጸመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ቤተ ክህነት ለማቋቋም ሲሰራ የቆየው የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ ያነሳቸው ችግሮች በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስር እንዲፈቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ዕርቅ መፈጸሙን ገለፀ።

ኮሚቴው ከጠቅላይ ቤተ-ክህነት ጋር የነበረው ልዩነት ባነሳቸው ችግሮች ሳይሆን በመፍትሔው ላይ እንደነበርም ተጠቅሷል።

ዕርቀ ሠላም እንዲፈጸም የሽምግልናውን ሚና የተወጣው ‘ጃን ትምህርትና ሠላም ለወገን’ የተሰኘ ሲቪክ ማኅበር ነው።

የማኅበሩ ሰብሳቢ ላዕከሠላም ባያብል ሙላቴና የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ለመመስረት ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ በላይ መኮንን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ላዕከሠላም ባያብል በመግለጫው ላይ እንዳሉት÷ የኦሮሚያ አካባቢ ቤተክርስቲያን አገልግሎት መዳከም ችግሩን መፍታት እንደሚገባ በአባቶች፣ በምዕመናንና በሊቃውንት ዘንድ ቢታመንበትም መፍትሔው ላይ ግን ልዩነቶችን እንደነበሩ አብራርተዋል።

በዚህም ላለፉት ስድስት ወራት በማህበሩ ሸምጋይነት የኮሚቴውን አባላት ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር በማነጋገር ችግሩን ለመፍታት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚህም በሁለቱም ወገን ስምምነት ተደርሶ ትናንት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ፀድቆ ዕርቅ መደረጉን አብስረዋል።

በመፍትሔውም በኦሮሚያ ክልል የቤተክርስቲያን መዳከም ችግርን ለመፍታት በጠቅላይ ቤተክህነት ስር በሚቋቋም ጠንካራ አካል በኩል በአንድነት ለመፍታት ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።

በስምምነቱ “አሸናፊዋ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ናት” ያሉት ሰብሳቢው የቤተ ክርስቲያን ልጆች በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

The post የኦሮሚያ ቤተ ክህነት በሚል የተቋቋመው ኮሚቴ ያነሳቸው ችግሮች በጠቅላይ ቤተ-ክህነት እንዲፈቱ ዕርቅ ፈጸመ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply