
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አባቶች ጋር በወቅታዊ የቤተክርስትያን ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ችግሮችን ለመፍታት ቃል የገቡ ቢሆንም አሁንም ችግሮች እንዳልተፈቱ እየተነገረ ነው :: የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ያቋቋመችው የሕግ ኮሚቴ አባል የሆኑት የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አያሌው ቢታኔ እንደተናገሩት፣ ፕሬዝዳንቱ በቤተክርስያን ጉዳይ የታሰሩ ሰዎች እስከ ዛሬ ማክሰኞ ድረስ ይፈታሉ ብለው ቃል የገቡ ቢሆንም፣ ሽንገላ የሚመስል ነገር እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ሕግን የማስፈጸም ግዴታ እያለባቸው ያለባቸውን ኃላፊነት ባለመወጣታቸው ምክንያት አሁንም በርካታ የሕግ ጥሰቶችና የንብረት ውድመቶች እየደረሱ እንደሆነ ጠበቃው ተናግረዋል፡፡ ትናንት ሰኞ በፍርድ ቤት እግድ የተጣለባቸውና ከቤተክርስትያኗ ቀኖና ውጭ የተሾሙ ግለሰቦች በአሰላ የአቡነ ያሬድ መንበረ ጵጵስናን ሰብረው የገቡ ሲሆን፣ ይህም በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ድጋፍ የሚደረግ ሕገ-ወጥ ድርጊት መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሻሸመኔና አርሲ ነገሌን ጨምሮ በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች አሁንም በርካታ ካህናትና ምዕመናን ያለምንም ጥፋት ታስረው ይገኛሉ ያሉት ጠበቃው፣ ከዚህ በፊትም በመንግሥት በኹለት ቀን ውስጥ ይፈታሉ ተብለው የነበሩ ታሳሪዎች ሳይፈቱ በርካታ ቀናት መቆጠራቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ራሱ ለገባው ቃል ተገዢ እየሆነ አይደለም ያሉት ጠበቃው፣ በዚህም ምክንያት ካህናትና ምዕመናን ለበርካታ ችግሮች ተጋልጠዋል ቤተክርስትያኗም ጉዳት እየደረሰባት ይገኛል ብለዋል፡፡ ጠበቃው አክለውም፤ ቤተክርሰትያኗ ከመንግስት ጋር የደረሰችው ስምምነት በመንግሥት በኩል ሊደረግ ታስቦ የነበረውን ሰልፍ የማስቀረት ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም ያሉ ሲሆን፣ አሁን ባለው ሁኔታ ችግሩ እየከፋ መሄዱን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመትን አከናውነዋል ካለቻቸውና ከተሾሙ አባቶች መካከል ይቅርታ ጠይቀው ወደ ቤተክርስትያኗ የተመለሱ መኖራቸው የሚታወስ ቢሆንም፣ ከተሾሙት ግለሰቦች መካካል አብዛኞቹ እስካሁን ድረስ በይፋ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ቤተ ክርስትያኗ ያልተመለሱ ሲሆን፣ በፍርድ ቤት የተጣለባቸውን እግድ በመጣስ ከመንግስት በተለይም በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ባሉ የጸጥታ ኃይሎች በመታገዝ ተዳጋጋሚ የሕግ ጥሰቶችን እየፈጸሙ ይገኛል፡፡ “ምዕመናኑ ምንም እንኳን በሚፈጸሙ ድርጊቶች ያዘኑ ቢሆንም የቤተክርስትያን አባቶችን ትዕዛዝ እየተጠባበቁ ይገኛሉ” ያሉት አያሌው፣ “መንግስት የገባውን ቃል አልመፈጸሙ፣ በሕግ እንዲያስፈጽም የተሰጠውን ኃላፊነት አለመወጣቱና የያዘው አካሄድ ሕዝብና አገርን ዋጋ የሚያስከፍል ነው” ብለዋል፡፡ ለዚህም እስከ ዛሬ ማክሰኞ ድረስ ኹሉንም ጉዳዮችና የሕግ ጥሰቶች ለማስተካከል በኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት ሽመልስ አብዲሳ የተገባው ቃል እንዲፈጸም የጠየቁት አያሌው፣ የቤተክርስትያን ጉዳይ ወደ ከፋ ነገር ሳያመራ መንግስት ኃላፊነቱን በአግባቡ እዲወጣ አሳስበዋል። © አዲስ ማለዳ “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post