የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የተፈጸመ ግድያ “በገለልተኛ አካል እንዲጣራ” ጥሪ አቀረበ። ፓርቲው ዛሬ እሁድ…

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የተፈጸመ ግድያ “በገለልተኛ አካል እንዲጣራ” ጥሪ አቀረበ።

ፓርቲው ዛሬ እሁድ ባወጣው መግለጫ “በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመውን ማንኛውንም ዓይነት ግድያ” አውግዟል።

ከአዲስ አበባ 80 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ከሚገኘው ገዳም የካቲት 12 ቀን 2016 “በታጣቂ ቡድኖች” ከተወሰዱ አምስት መነኮሳት መካከል አራቱ መገደላቸውን፤ አንድ መቁሰላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የኦሮሚያ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ለግድያው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት “ኦነግ ሸኔ” የሚሉትን እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን ተጠያቂ አድርጓል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ዛሬ እሁድ ባወጣው መግለጫ በካህናቱ ላይ  “የጅምላ ጭፍጨፋ” ላለው ግድያ የኦሮሚያ ክልል፣ የፌድራል መንግሥት እና መዋቅሮቻቸው “ኃላፊነት መውሰድ” እንደሚኖርባቸው አሳስቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት “እንዲህ አይነት የወንጀል ድርጊቶችን በመወቃቀስ እና በመሸፋፈን ማለፉን አቁሞ በምርመራ እንዲጣራ ጉዳዩን ለገለልተኛ አካል ክፍት ማድረግ አለበት” ኦነግ ጥሪ አቅርቧል።

ፓርቲው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ  “ለሚደረገው ገለልተኛ ምርመራ መተባበር አለበት” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። 

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በዛሬው መግለጫው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን “አንዳንድ አባላት እና መሪዎች በትግራይ ጦርነት ወቅት ሁኔታውን ከማቃለል እና መፍትሔ ከመሆን ይልቅ ግጭቱን ለማቀጣጠል የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል” ሲልም ከሷል።

“በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የተፈጸሙ አሰቃቂ የአየር እና የሰው አልባ አውሮፕላን ድብደባ እና የጅምላ ግድያ ቤተክርስቲያኒቱ ከማውገዝ ተቆጥባለች ወይም መርጣ ተናግራለች” ያለው ኦነግ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን በሀገሪቱ እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች እና ኹከቶች ውስጥ እንደ ሠላም ፈጣሪ አካል የምትጫወተውን ሚና እንደገና እንድታጤን” ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

Twitter https://twitter.com/EthioFM

YouTube https://www.youtube.com/@onelovebroadcast/videos

Facebook  https://www.facebook.com/onelovebroadcast

Source: Link to the Post

Leave a Reply