የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ጥቃት ሰነዘሩ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 19 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ገደብ ከተማ ላይ ጥር 17 ለጥር 18/2015 ዓ/ም አጥቢያ ለሊት ጥቃት መሰንዘራቸውን ገልጸዋል። ታጣቂዎቹ ጥር 17/2015 ዓ/ም ከለሊቱ 6 ሰዓት ወደ ከተማዋ በመግባት ተኩስ የከፈቱ ሲሆን በዚህም በከተማዋ የሚገኙት የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱን ለመከላከል ሙከራ ቢያደርጉም ነገር ግን ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ ለማፈግፈግ ተገደዋል ነው የተባለው። የገደብ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ንብረት የሆኑ ከ ሰባት በላይ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶችንም ያወደሙት ታጣቂዎቹ ማረሚያ ቤት በመስበር እስረኞችን ማስለቀቃቸውን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማዋ ባለስልጣን ለአማራ ድምፅ አረጋግጠዋል። ታጣቂዎቹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አቢሲኒያ ባንክ ላይ ዝርፊያ የፈፀሙ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የንግድ ተቋማትን መዝረፋቸው እና በእሳት ማቃጠላቸው ተጠቁሟል። ጥቃቱ የመንግስታዊ መዋቅር ድጋፍ ያለው ይመስላል ሲሉ ሀሳባቸውን ለአማራ ድምፅ ያጋሩት ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ታጣቂዎቹ ወደ ከተማዋ ከመግባታቸው ውስን ሰዓታት ቀደም ብሎ በአከባቢው የኔትዎርክ አገልግሎት መቋረጡን ገልፀዋል። ታጣቂዎቹ የከፈቱት ጥቃቱ ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት የዘለቀ ሲሆን በዚህም የተገደሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸው ተመላክቷል። ዘገባው የአማራ ድምፅ ሚዲያ ነው።
Source: Link to the Post