የኦነግ የጦርነት ዐዋጅ! – አደፍርስ ኢብሣ  (ከአዲስ አበባ)

ካለፉት ጥቂት ቀናት ወዲህ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የሚሰማው ነገር ጤና የሚሰጥ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ የኅሊና ሰላምና የአእምሮ ዕረፍት አጥቷል፡፡ ከአንዱ የመከራ አዙሪት ስንወጣ ሌላውና ምናልባትም የባሰው እየተተካ የዕዳ ደብዳቤያችን ከመቀደድ ይልቅ እየታደሰ የሄደ ይመስላል፡፡ አሁን ፍራቻው ለዐይን ይበጃል ያሉት ኩል ዐይንን ጨርሶ እንዳያጠፋ ነው፡፡ መፍራት አሁንና አሁንን ነው፡፡ አፈሩ ይቅለላቸውና እማማ ደብሬ “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” ይሉ ነበር፡፡

ይሄ የጉሮ ወሸባየ ነገር ደግሞ ጉድ እያፈላ ነው፡፡ አንዱን ጀግና ተቀብለን ሳንጨርስ ሌላውን ጀግና በድምቀት የመቀበል ሥራ ወጥሮ የያዘን ከመሆኑም በተጨማሪ አንደኛው ጀግና በሌላኛው ጀግና የአቀባበል ድምቀት የተበለጠ እየመሰለው ሳይሆን አይቀርም ጀግና ለጀግና መከባበር ቀርቶ ወጥመድ መዘርጋትን ሥራየ ብሎ ተያይዞታል፡፡ ሌላው እየገረመኝ የመጣ ጉዳይ ከስደትና ከቤተሰብ ናፍቆት ርቆ ቆይቶ ወደ ሀገር መምጣት ከቁም ነገር ተጥፎና ወደ ሀገር መግባት ብቻውንና በራሱ እንደትልቅ ድል ተቆጥሮ በፈረንጅኛው አነጋገር ይህን ያህል ለ”simple psychology” መንበርከክ አሣፋሪ ሊሆን ያልቻለበት ምክንያት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ለይቶልን ተፈጥሯዊ ጠባያችን ሳይለወጥ አልቀረም፡፡ ከጦር ግምባር በአንጸባራቂ ድል ብንመለስ ወይም የሀገሪቱን ከፍተኛ ሥልጣን ብንይዝ ምን እናሳይ ይሆን? በብዙ ወቅታዊ ገጠመኞች ማፈሬን ሳልገልጽ ባልፍ ራሴን እታዘበዋለሁ፡፡ እናም አፍሬ በማላውቀው ሁኔታ አፈርኩ፡፡ ዋናው የሀፍረቴን ምንጭ ግን ወረድ ብዬ እገልጣለሁ፡፡ “በሰላም ወደ ሀገር ገብቶ በሰላም በሚኖር ሰላማዊ ሕዝብ መሀል ሁከት መፍጠርን ምን አመጣው?” ብዬ ሁለተኛውን የሀፍረት መንስኤ አሁን እዚህ ላይ መናገር ግን አልፈልም፡፡(በዚህች ቅጽበት ፍል ውኃ አካባቢ ከአምስት ሰዎች በላይ መሞታቸውን አንድ ጓደኛየ በስልክ ነገረኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ እባክህን አንተ እንኳን አትተወን፡፡ እባክህን በቃችሁ በለን፡፡ እንደሚባለው አንተም አበሻ ሆንክ ማለት ይሆን?)

ኦነግ ከአሥመራ ሲመጣ ከጦር ሜዳ ድል አድርጎ የገባ ይመስል ያ ሁሉ እርኩቻ ታዬ –  ለዚያውም ኢትዮጵያ ወደምትባል የብዙኃን አገር ሳይሆን ኦሮምያ ወደምትባል ሪፓፕሊክ እንደገባ ያህል እስኪቆጠር ድረስ፡፡ ሌላውም እንደዚሁ በግልም ሆነ በቡድን ወደ ሀገር ሲገባ አቀባበሉ ከጦር ዐውድ በድል አድራጊነት የመጣ ያህል ነው፡፡ ካለፈው ቅዳሜ መስረም 5/2011 በፊት የነበሩት አቀባበሎች ገብስ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹን እኔም ተገኝቼባቸዋለሁ፤ ደስ ይሉ ነበር፡፡ በሚዲያም በጉጉት የተከታተልኳቸው አሉ፡፡ የቅዳሜው ግን ሀገሪቱን ወደ ገደል የሚከት ጣጣ ተከትሎት መጥቷል ወይም እዚሁ ተሰናድቶ ሲንተከተክ ኖሯል፡፡ከዚያም በኋላ ነው አቀባበልን የጠላሁትና የሰለቸኝም፡፡

በቅድሚያ አንድ ነገር ልበል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ድፍረቴ ይቅርታ ይደረግልኝና ኢቲቪ የኦነግ ምሽግ በሌላ አነጋገር ደግሞ ኦኤምኤንና ኦቢኤን ሳይሆን አልቀረም፡፡ ማስረጃየን እንካችሁ፡- በአንድ ጥናታዊ ዘገባ መሠረት መስቀል አደባባይ ከነስድስቱም መውጫ በሮቹ ጋር በሰው ግጥም ብሎ ቢሞላ ሊይዝ የሚችለው የሕዝብ ብዛት 800 ሽህ ገደማ እንደሆነ ሲወራ ሰምቻለሁ፤ እኔም በሌላ ቦታ ባደረግሁት አንድ አነስተኛ ቅኝት ያን ጥናት አምኜበታለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሚያዝያ 29/1997 ለመለስ ከተደረገ የድጋፍ ሰልፍ አንስቶ ብዙ ተሸውደናል ማለት ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ግን የበቀደሙ ቅዳሜ ሰልፍ የሕዝብ ብዛት በኢቲቪ የተገለጸበት ሁኔታ ነው፡፡ ኢቲቪ ቅንጣት ሳያፍር የሰውን ብዛት “ከ4 ሚሊዮን በላይ” ብሎት አረፈው፡፡ ሲዋሽ ለከት ሊኖር ይገባል፤ እንደጣቃ መተርተር ለትዝብት ይዳርጋል፡፡ የሚወዱትን አካል ወይም ሰው ለመጥቀምና ለመደገፍ ታስቦ የሚሠራ ነገር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንዳያመዝንም መጠንቀቅ ተገቢ ነው – ለምሣሌ እኔ ኢቲቪን ክፉኛ ታዘብኩት፤ በዚህም ኦነግ አልተጠቀመም እላለሁ፡፡ በዚያ ሰልፍ ላይ ከወጪ ቀሪ 500 ሽህ ሕዝብ ተገኝቶ ከሆነ ጥሩ ነው – ግፋ ሲልም አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ከወጣ እሰዬው – በበኩሌ ደስ ይለኛል፡፡ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚኖርባት በወያኔ በሚነገርላት አዲስ አበባ ውስጥ እንዴት ነው በአንድ ሰልፍ 4 ሚሊዮን ሕዝብ ሊገኝ የሚችለው? አሃ! እየተስተዋለ እንጂ ጎበዝ፡፡ ለምን እንደሚዋሽ ደግሞ ፈጽሞ አይገባኝም – ደግሞም ተደመረ በተባለ የሕዝብ ንብረት ኢቲቪ እንዲህ ሲዋሽ “ዋጮን ቢገለብጡት ያው ዋጮ ነው” እንደተባለው ሆነብኝ፡፡ ለነገሩ 50 ሚሊዮን ቢባልም ሆነ በርግጥም ያንን ያህልና ከዚም በላይ ሕዝብ በሰልፉ ላይ ቢገኝ ደስ ይለኛል እንጂ አልከፋም፡፡ የበዛ ውሸት ግን ብዙ አንድምታዊ ነገሮችን ጠቋሚ ነውና በሌላ ነገር ያስጠረጥራል፤ በአጭሩ “መስቀል አደባባይ አራት ሚሊዮን ቀርቶ አንድ ሚሊዮንም አይዝም” ነው ክርክሩ፡፡ በትንሹ ያልታመነ ደግሞ በትልቁም አይታመንም፡፡

የበቀደሙን ኦነግን የመቀበያ ሠልፍ ተከትሎ አዲስ አበባና አካባቢዋ ሰላም ያጡት ጉዳይ በጥልቀት መጤን አለበት፡፡ ተጢኖም አስቸኳይ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል፡፡

ይቺ ሁሉንም የጥፋትና የሁከት ድራማ ወደ ሕወሓት የማላከክ ነገር አታዋጣም፡፡ “ቤታቸውን ከፍተው ሰው ሌባ ይላሉ” ይባላል፡፡ የራስን ስህተት ወይም ቅርብ በሚገኝ አካል የሚፈጠርን ማህበራዊና ፐለቲካዊ ቀውስ በሰው ላይ መለጠፍ ስህተት ነው – ምንም እንኳን የወደቀ ግንድ ምሣር እንደሚበዛበት የታወቀ ቢሆንም፡፡ እንዲህም ሲባል ወያኔ ይህን መሰሉን የጥፋት ወጀብ አይጠቀምበትም ለማለት አይደለም፡፡ ወያኔዎች ከፀሐይ በታች የሚገኝን የጥፋት ዘዴ ሁሉ ከመጠቀም አይመለሱም፡፡ እንኳንስ በዓላማ አንድነት ተቆራኝተዋቸው በነፃ አግዘዋቸው ይቅርና የጥፋት እገዛንና ትብብርን በሚሊዮኖችና ቢሊዮኖች ብር ለመግዛት ወያኔዎች አያቅማሙም፡፡ አስፖንሰር እያደረጉ በሚያቀጣጥሉት ረብሻም ሆነ እነሱ ኮትኩተው አሳድገውና በሁለንናዊ ድጋፍ አስታጥቀው ያሠማሩት በደምብ የምናውቀው ሌላው ኃይል ጃዝ እያለ በሚለቃቸው ወጣቶች በሚደረግ ግድያና ዘረፋ መላው የትግሬ ዘር ቢያልቅ እንኳ እነሱ ደንታቸው አይደለም፤ የተመረዙበትና በጠማማ ቀን የተለከፉበት የሀብትና የሥልጣን ሱስ ከነሱ እጅ ከሚወጣና አማራ የሚባል ሕዝብ ከታወጀበት ሕወሓታዊ ጄኖሳይድ እፎይ ከሚል ዓለም ብታልፍም ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ወንድሞቼ – ጥላቻ መጥፎ ነው፡፡ ጥላቻ ቂምን እየወለደ፣ ቂምም በቀልን እያፈራ ልክ እንደወያኔ ዕንቅልፍ ለሚያሳጣ የመከራ ሕይወት ይዳርጋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁሉ ይልቅ ራስን መለወጥ እጅግ ከባድ ቢሆንም የሚያዋጣን ፍቅር ብቻ ነውና ሸፋፋና ወልጋዳ የጥላቻና የበቀል አስተሳሰባችንን ለውጠን በሰውነታችን ብቻ እንፋቀር፡፡… የእግረ መንገድ ምክር፡፡

ትልቁ ችግራችን የሚመስለኝ ኢትዮጵያ በሁለት አጠባቂኞች ውስጥ መግባቷ ነው – ወያኔና ኦነግ፡፡ የነዶ/ር ዐቢይ ጎራ ደግሞ “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥል” ዓይነት መሆኑ ሌላው ህመም ነው፡፡

አሁንም ይቅርታ ይደረግልኝና ኦነግ በመንታ ምላስ የሚንቀሳቀስ እስስታዊ ፍጡር ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ኦነግን ማመን እያስቸገረኝ መጥቷል፡፡ የለማ ቡድንም ፈራው፤ የመንታ እናት ተንጋላ ታጠባ እንዲሉመ ሆኖባቸው የተቸገሩ ይመስላል፡፡ የአሁኑ አጣብቂኝ ግን አንዱን እንዲመርጡ ያስገድዳል፡፡ አለበለዚያ እነሱ “ፍቅር ፍቅርና መደመር መደመር” ሲሉ ይህን ተስፋ ሰጪ የነበረ ለውጥ አንዳች ማዕበል መጥቶ እንዳይሞጨልፈው፡፡ ያኔ ጸጸትና ጥርስን ማፋጨት አይጠቅምም፡፡

ከታዘብኩት፡-

አንደኛ – በቅዳሜው ሰልፍ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ ኦነግ የርስ በርስ ጦርነት ዐውጇል፡፡ Literally speaking, OLF has declared civil war upon the residents of Addis Ababa through its spokesperson at the rally. ይህንን ዐዋጅ ደግሞ የለውጡ ኃይል የተቃወመ አይመስለኝም፡፡ ይህን ግልጽ የጦርነት ዐዋጅ አለመቃወም ደግሞ አንድም ፍርሀት ነው፤ አንድም የታወጀው ጦርነት መንግሥታዊ ድጋፍ አለው፤ አንድም … እያለ የሚቀጥል የአንድምታዎች ምንዛሬ አለው፡፡ በጥቅሉ የነገሮች አካሄድ አላማረኝም፤ አልገባኝምም፡፡ አዲስ አበባ ዕረፍት ያጣችውም ከዚያን ዕለት ወዲህ ነው፡፡ ለማስረጃ ያህል የዐዋጁን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

የኦነግ አባል እንደሆነ የሚነገርለት የቀድሞ ጋዜጠኛና የዕለቱ የዝግጅት አስተባባሪ (ማስተር ኦፍ ሴረሞኒ) እንዲህ አለ – ሕዝቡም በከፍተኛ ስሜት ተውጦ አስተባባሪው የሚወደውን መልስ መለሰ ፡-

አስተባባሪው – ፊንፊኔ የማን ናት?

ሰልፈኛ – የኦሮሞ!

አስተባባሪ – ፊንፊኔ የማን ናት?

ሰልፈኛ – የኦሮሞ!

አስተባባሪ – እናስመልሳታለን!

ሰልፈኛ – እናስመልሳታለን!

ዕጥር ምጥን ያለችና ሀተታ ያልበዛባት ዐዋጅ ናት፡፡ እንደዚች ያለች ቅልብጭ ያለችና ውጤቷም በደቂቃዎች ውስጥ መታየት የጀመረ ዐዋጅ አይቼም ሆነ ሰምቼ አላውቅም፡፡ እንዲህ ነን እኛ፡፡ ጥሬ ሲሉን ብስል፤ ብስል ሲሉን ጥሬ፡፡ ግን ግን አዲስ አበባ ማለትም ፊንፊኔ ከየት ነው የምትመለሰው? የአዲስ አበባ ኗሪ ጉድሽ! እየመረጠ ከሚገድል በጅምላ ወደሚ… ለነገሩ ምን አገባኝ!

ሁለተኛ – ኦነግ ዓርማ አለው፡፡ ያ ሁሉ ሰልፈኛ የኦነግን ዓርማ መያዙ አስደሳች ነው – እንደ ኦነግና ኦነግነት፡፡ ግን ኦነግ የተደመረው ከኦሮሞ ጋር ሳይሆን ከሌሎች ጋር ነው – ኦሮሞ ከኦሮሞማ ዱሮውን የተደመረ ነው፡፡ ስለዚህ ኦነግ ከሌሎች ጋር ሊደመር ከመጣ ቢያንስ መድረኩ አካባቢ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሊወክል የሚችል ምልክት – የሚጠላውም ቢሆን ለፖለቲካዊ ሥልት ሲል – ቢያውለበልብ የሌሎችን ቀልብና ወዳጅነት ያገኛል እንጂ አይጎዳም ነበር፡፡ በፍቅር እንደመር ለሚለን ወንድም እንደዚያን የመሰለ ፍጹም ጥላቻ ለሌሎች ማሳየት ብልኅነት አይደለም፤ ወዳጅነትንም ይሸረሽራል፡፡ ፖለቲካ ብስለትንና ከሁኔታዎች ጋ መለወጥን ይጠይቃል፡፡ በዚያ ድርጊት ሕወሓትና ኦነግ አንድ ሆኑብኝ፡፡ ለነገሩ tigraionline.comን በሰሞኑ ዝግጅቶቹ ለሚጎበኝ ይህን ሥልታዊ አንድነት በግልጽ ይታዘባል፡፡ ታየኝ – ትግራዋይ ኦሮሞን ወድዶ የኦነግን ዓርማ በፍቅር አንገቱ ላይ ሲጠመጥም፡፡ ጉድ እኮ ነው ዘንድሮ፡፡ እንዲህ የምለው ከአንጀቴ እውነቴን እንጂ ያን ከዚህ ወይ ይህን ከዚያ ለማቃቃር አስቤ እንዳይመስላችሁ፤ በፍጹም – ፍርፍር ብዬ የሣቅሁበትን የማይገጣጠሙ ነገሮችን መገጣጠም ታዝቤ ሳበቃ ነው እንዲህ የምለው፡፡ ይልቁንስ አዳሜ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ምንትስ እየተባባልሽ ዕድሜሽን አታሳጥሪ፤ ሀብት ንብረትሽንም በመልቲዎች አታስመዝብሪ፡፡ ብትችይ በአንድነት በፍቅር ኑሪ፡፡ አንድ ላይ መኖር ካቃተሸም ተፋቺና ለየብቻሽ በሰላም ኑሪ፤ መለያየት ሞት የሚሆነው በዘፈን እንጂ በገሃዱ ዓለም አይደለምና ይህንንም አማራጭ ሞክሪው፡፡ ከሁልጊዜ ፈስ የአንድ ቀን ምንትስ ይባላል፡፡ እንዲህ እየተጃጃሉ ከመኖር በቅጡ ተለያይቶ በሦስት መንግሥታት ሥር መኖርም አዋጪ ነው – እንደኔ ግምት፡፡ በማትረባ ሚስት ዘወትር ከመቃጠል፤ በማይረባ ባል ዕድሜ ልክ ከመንገብገብ ተፋትቶ ሕይወትን በየግል ከእንደገና ማየት፡፡ አስቡብት፡፡ እኔ የዚህች አገር ታጥቦ ጭቃ ፖለቲካ እጅግ ሰልችቶኛልና ይህንንም እንሞክረው ባይ ነኝ – ደግሞስ ጊዜ ካለን አይደል!

 

በነጠላ ጫማ ባንቺ አረማመድ

እንዴት አለቀልሽ ያ ሁሉ መንገድ፡፡

አለ አሉ አንዱ ብሶተኛ፡፡ በዚህ አካሄዳችን ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ ልንገነባ! ቂቂቂቂ………..

ልዩ ማስታወሻ – በቀደም ቅዳሜ የሰልፉ ዕለት የሆነ ነገር ነው – ከሆኑት እጅግ ዘግናኝ አሳዛኝ ነገሮች ውስጥ አንዱን ብቻ ነው የምናገረው፡፡ ወጣት ኦሮሞዎች ሰበታ አካባቢ አንዱን አይሱዙ የጭነት መኪና ያስቆሙታል፡፡ ወደ መስቀል አደባባይ እንዲጭናቸው ያስገድዱታል፡፡ 2000 ሽህ ብር ክፈሉኝ ይላቸዋል፡፡ “3000 ብር እንከፍልሃለን” ይሉትና ከአፍ እስከገደፉ ሲጥ ብለው ይጫናሉ፡፡… ሲመልሳቸውና ክፈሉኝ ሲላቸው ደብድበው ሽባ ያደርጉታል፡፡ “ሳትሞት የማርንህም ወስደህ ስላመጣህን ነው” ብለው ውኃ በማያሰኝ ቁድራ ነርተው ነርተው አስተኝተውት ይሄዳሉ፡፡ የዘር ፖለቲካ እንዲች ነች፡፡ ነፍስ ይማር ሀገሬ ኢትዮጵያ፤ መልካም ዕድል ተረኛው ኦነግ፡፡ እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡… አዲስ አበባ አሁን እየታመሰች ነው … ወደቤቴ እንዴት እንደምገባ አላውቅም … ቤቴ ከከተማ ወጣ ይላል፡፡

 

Leave a Reply