የከምባታ ጠምባሮ እና የካፋ ዞን ለመከላከያ ሠራዊት 420 ሰንጋ፣ ፍየል እና በጎች አበረከቱ

የከምባታ ጠምባሮ እና የካፋ ዞን ለመከላከያ ሠራዊት 420 ሰንጋ፣ ፍየል እና በጎች አበረከቱ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የከምባታ ጠምባሮ እና የካፋ ዞን ሀገር የማዳን ተልዕኮውን እየተወጣ ላለው መከላከያ ሠራዊት 420 ሰንጋ፣ ፍየል እና በጎች አበረከቱ፡፡
በከምባታ ጠምባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ መኔዶ የተመራው የልዑካን ቡድን 264 ፍየሎች፣ 101 በጎች እና 24 ሰንጋዎች በሀገር ደረጃ ለተቋቋመው የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክቧል።
በርክክቡ ወቅት የተገኙት የመከላከያ ሚኒስትር ዲዔታ ወይዘሮ ማርታ ሉጂ እና የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊት በተደረገው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልፀው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተያያዘም የካፋ ዞን ነዋሪዎች እና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ 31 ሰንጋዎችን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት በስጦታ አበርክተዋል፡፡
ድጋፉንም በካፋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይ ተሠማ የተመራ ልዑካን ቡድን አማካኝነት ስጦታውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረክቧል፡፡
ምክትል ዋና አስተዳዳሪው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በአርሶ አደሩ ማሳ በመገኘት የልማት ስራን የሚሠራ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት የሚጠግን፣ በተለያየ መንገድ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ደም የሚለግስ፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያስከብርና ለህይወቱ የማይሳሳ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ አለኝታና መኩሪያ መሆኑን ጠቅሰው፥ ስግብግቡ የሕወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት የካፋ ዞን ህዝብ ያወግዛል ብለዋል፡፡
አቶ በላይ አያይዘውም የጁንታው ቡድን ህይወቱን ለሃገር አሳልፎ በሚሰጠው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በማድረስ ወደ ዝርፊያ መግባቱ እጅግ አሳፋሪና አረመኔያዊ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የካፋ ዞን ህዝብ የሀገሪቱን አንድነት ለማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን የሚያጠናክርበት ጊዜ መሆኑን በመጥቀስም መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና የዞኑ ህዝብም ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን የሚቆም መሆኑን መግለፃቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

The post የከምባታ ጠምባሮ እና የካፋ ዞን ለመከላከያ ሠራዊት 420 ሰንጋ፣ ፍየል እና በጎች አበረከቱ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply