
የከተራ እና የጥምቀት በዓል በድምቀት በተከናወነበት ጎንደር የቅዱስ ሚካኤል ታቦትን በከፍተኛ እጀባ፣ ወረብና ዝማሬ በማጀብ ወደ መንበራቸው በሰላም ለማስገባት ተችሏል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 12 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የከተራ እና የጥምቀት በዓል በከፍተኛ ድምቀት በተከናወነበት ጎንደር ከተማ ዛሬ ጥር 12 ደግሞ በጥምቀተ ባህር የነበሩ ሁለት የቅዱስ ሚካኤል ታቦታትን በክብር ወደ መንበራቸው ለማስገባት ተችሏል። ሀይማኖታዊ ስነ ስርዓቱን፣ የአካባቢውን ወግ እና ባህል በጠበቀ መልኩ የተከናወነውን የከተራ ብሎም የጥምቀትን በዓል ተከትሎ በርካታ ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባህሩ እንዲወርዱ መደረጉ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም ጥር 11/2015 የጥምቀት በዓል በከፍተኛ ድምቀት ከተከናወነ በኋላ አመሻሹን በርካታ ታቦታት ወደ መንበራቸው በእጀባ፣በጭብጨባ፣በወረብ፣በዝማሬ እና በባህላዊ ጭፈራ ታጅበው ወደየመንበራቸው መመለሳቸው ይታወሳል። በጥምቀተ ባህሩ ያደሩ የአጣጣሚ እና የፊት ሚካኤል ታቦታትም ዛሬ ጥር 12/2015 ወደ መንበራቸው ተመልሰዋል። ከንጋት ጀምሮ በሚያምር ወረብ፣ በዝማሬ እንዲሁም በሌሎች ሀይማኖታዊ ስርዓቶች፣በባህላዊ ጭፈራ እና እጀባ ታቦታት ለመሸኘት ብሎም ወደ መንበራቸው ለመመለስ ተችሏል። ታቦታት ወደ መንበራቸው መግባታቸውን ተከትሎ መልዕክት ያስተላለፉ አባቶችም አጠቃላይ ከከተራ እስከ ጥምቀት የነበረውን ሂደት በእጅጉ ያደነቁ ሲሆን ባህላዊ የአለባበሳችን ስርዓት የተመለሰበት ቀን ሲሉም ጠርተውታል። ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ አስፈላጊ ነገሮችን በማሟላት ረገድ ሁሉም በየዘርፉ ላሳዬው በጎ አስተዋጽኦም ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። በጎንደር እና አካባቢው በአጠቃላይ 1,700 ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት የከተራ እና የጥምቀት በዓልን በሰላም ማከናወናቸው ተገልጧል፤ ለሀይማኖት አባቶችና ለምዕመናን በጥቅሉ ለተሳታፊዎች ሁሉ ምስጋናም ቀርቦላቸዋል። በቀጣይም አበራ ጊዮርጊስ ስባረ አጽም ጥር የፊታችን ጥር 18፣ ሎዛ እና ቤዛዊት ማርያም ጥር 21 በአካባቢያቸው እንዲወጡ ተደርጎ በዓሉ ከተከበረ በኋላ ወደ መንበራቸው የሚመለሱ ይሆናል። በተመሳሳይ ጭርቆስ፣ ሩፋኤል እና ተክለ ሀይማኖት በንግሳቸው በአካባቢያቸው እንዲወጡ ብሎም በዓሉ እንዲከበር ከተደረገ በኋላ ተመልሰው ወደ መንበራቸው እንደሚገቡ አሚማ ያነጋገራቸው አባቶች ተናግረዋል።
Source: Link to the Post