የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ ስድስት የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ ወሰደ፡፡

የእውቅና ፍቃድ ሳያገኝ በድህረ ምረቃ እና በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ተማሪዎችን ሲያስተምር የነበረው “ሲፈን ኮሌጅ” እንዲዘጋ ተማሪዎቹንም እንዲበትን የተወሰነበት  መሆኑን በኤጀንሲዉ የእዉቅና ፍቃድ እና እድሳት ዳሬክተር አቶ አብይ ደባይ ለአሀዱ ተናግረዋል፡፡

ሲፈን ኮሌጅ አዲስ አበባ ጀሞ አካባቢ በከፈተው ካምፓስ በማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በድህረ ምረቃ ደረጃ፣ በአካውንቲንግ ፋይናስን እና አድሚኒስትሬሽን በቅድመ ምረቃ ሲያስተምር ተደርሶበታል ብለዋል።

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ሲፈን ኮሌጅ እውቅና እንዲሰጠው ቢጠይቅም ዝቅተኛውን መስፈር ማሟላት ባለመቻሉ ማስተካከል ያለበትን ጉዳይ እንዲያስተካክልና በሶስት ወራት ውስጥ እንዲያሳውቅ ተነግሮት እንደነበር ገልጸዋል።  ሆኖም ኮሌጁ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች መዝግቦ ሲያስተምር በድንገተኛ ክትትል ተደርሶበት እርምጃ እንደተወሰደበት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ዲላ የሚገኘዉ ፓራዳይዝ ቫሊ ኮሌጅ እዉቅና ሳይኖረዉ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር እና በማስመረቅ ላይ በመሆኑም ለሁለት አመት በፋርማሲ ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ እንዳያስተምር እገዳ እንደተጣለበትም ገልጸዋል፡፡

ግሬት ላንድ ኮሌጅ ከእዉቅና ዉጪ በመቱ እና በደሌ ከተሞች ላይ ያለፍቃድ በመክፈታቸዉ እንዲዘጉ መወሰኑንም አቶ አብይ ለአሀዱ አረጋግጠዋል፡፡በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመማር የሚመዘገቡ ተማሪዎች ተቋሙ የምዝገባ ፍቃድ እንዳለው ማረጋግጥ አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።

ቀን 30/07/2013

አሐዱ ራድዮ 94.3

The post የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጀንሲ ስድስት የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ ወሰደ፡፡ appeared first on አሐዱ ራድዮ 94.3 እና ቴሌቪዥን.

Source: Link to the Post

Leave a Reply