የካራማራ ድል፡ እንደ አድዋ፤ ትልቁ የኢትዮጵያውያን የጋራ ድል

ከ46 ዓመታት በፊት የካቲት 26 ቀን 1970 የኢትዮጵያ ጦር ድንበር ጥሶ ወደ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት የገባውን የሶማሊያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ግዛት በማስወጣት ካራማራ ተራራ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ማወለብለቡን ታሪክ ያወሳል፤ ያስታውሳልም።

የካራማራ ጦርነት ከአድዋ በኋላ በታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪ እንዳትደፈር ታላቅ ጀግንነት የታየበት እና እጅግ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት ውጊያ ነበር። ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከሀምሌ 1969 እስከ መጋቢት 1970 ባለው ጊዜ በግምት ከ60 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተለያዩ የምስራቅ ጦር ግንባሮች ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት ተሰውተዋል።

መስዋዕትነታቸው ከደርግ ውድቀት በኋላ በመንግስት ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል። አሁንም የትኩረቱ ጉዳይ አጠያያቂ ነው። በ1950ዎቹ መጀመሪያና አጋማሽ ላይ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡ ሲሆን የጣሊያን ሶማሊላንድ እና የብሪቲሽ ሶማሊላንድም ነጻ ወጥተው የሶማሊያ ሪፐብሊክን መስርተዋል።

ቀጥሎም በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በጅቡቲ እና ሪፐብሊክ በመሰረቱት ሁለቱ ሶማሊላንድ ስር የሚገኝ መሬት “የታላቋ ሶማሊያ” ነው የሚል ህልም ይዘው ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬት ላይ አጠቃላይ ሐረርጌን፣ ባሌን፣ አርሲን፣ ሲዳማንና ከፊል ሸዋን ለመጠቅለል የሚያስችል አዲስ ካርታም አዘጋጅተው ነበር።

በዚህም በወቅቱ ነጻ አገር የነበረችው ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ የሰርጎ ገብ ጥቃቶችን ይፈጽሙ የነበር ሲሆን፤ ለአብነት በ1953 በኢትዮጵያ የተከሰተውን የታህሳስ ግርግር ተከትለው እንዲሁም በ1959 ከደፈጣ ጥቃት እስከ መጠነ ሰፊ የወረራ ሙከራ አድርገዋል። ኾኖም በጊዜው ቀጠናውን ይጠብቅ በነበረው ሌተናል ጀነራል አማን ሚካኤል የሚመራው 3ኛው ክፈለ ጦር ተመትተው ተመልሰዋል።

በኋላም በ1962 ወታደሩ ጀነራል መሀመድ ዚያድባሬ በመፈንቅለ መንግስት የሶማሊያን መንግስት በትረ ስልጣን በመጨበጥ ‘የታላቋ ሶማሊያ’ ህልማቸውን በይፋ ገልጸው ወታደራዊ ዝግጅት ማድረግ ጀምሩ። በወቅቱ ኢትዮጵያ የየካቲት 1966 አብዮትን ተከትሎ ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ከስልጣን አውርዶ ስልጣን የተቆጣጠረው ደርግ በሰሜን ነፍጥ አንስቶ የሚታገለው ሻዕቢያና ጀብሃ፣ ኢዲዩ በጎንደር፣ ህወሐት በትግራይ መንግስትን በመፋለም ላይ ነበሩ።

እንዲሁም በመሀል አገር እና ሌሎች አካባቢዎች ኢህአፓና ደርግ በነጭ ሽብርና በቀይ ሽብር ደም መፋፈስ ውስጥ የነበሩበት ወቅት ነበር። በአጠቃላይ ዚያድባሬ ግዙፍ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ ደርግ ግን ከንጉሱ የተቀበለው አራት ክፍለ ጦሮች ብቻ ነበሩት። የጦርነቱ ውጥረት እያየለ ሲመጣ የተለያዩ የማሸማገል ጥረቶች በተለያዩ አካላት የተደረጉ ሲሆን፤ በመጨረሻም የኩባው ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለማርያምንና ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬን የደቡብ የመን ዋና ከተማ በሆነችው ኤደን ላይ አገኟቸው። 

በኤደን የተደረገው ውይይት በዚያድባሬ ፍቃደኛ አለመሆን ያለ ውጤት ከተበተነ በኋላ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ለመጪው ውጊያ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተገነዘቡ። በዚህም ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማሪያም “አገርህን፣ ህልውናህን እና አብዮትህን አድን፤ ተነስ! ታጠቅ! ዝመት! እናሸንፋለን!” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላለፉ።

ጥሪውን የሰማው የአዲስ አበባ ህዝብም ድጋፉን ሚያዚያ 6 ቀን 1969 በአብዮት አደባባይ ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ገለጸላቸው። በክፍለ አገር ከተሞችም የድጋፍ ሰልፎች ተደረጉ። በቀበሌ ደረጃ በተዋቀሩ የእናት ሀገር ጥሪ አስተባባሪ ኮሚቴዎች አማካኝነትም ለሠራዊቱ ስንቅ የሚሆኑ ደረቅ የምግብ ዓይነቶችን በሶ፣ ቆሎ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ብስኩት የመሳሰሉትን ማዘጋጀት ተጀመረ።

ጥሪውን ተከትሎ ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት 300 ሺህ የሚሆን ህዝባዊ ሰራዊት በወቅቱ በተቋቋመው ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ ወደነበረው ‘ታጠቅ’ ገቡ። ኢትዮጵያ የስልጠና ዝግጅቷን ካጧጧፈች በኋላ ሰኔ 19 ቀን 1969 ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቅ ወታደራዊ ሰልፍ አሳየች።

ለተከታታይ 10 ዓመት ሲሰለጥን የነበረው የዚያድ ባሬ ኃይል ሐምሌ 3 ቀን 1969 ላይ በኦጋዴን ክልል ላይ ተራርቀውና መረዳዳት በማይችሉበት ሁኔታ የነበሩ የ3ኛ ክፍለ ጦር አካል የሆኑትን የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊቶች መግፋት ጀመረ። በዚህም በምስራቅ 700 ኪሎ ሜትር በደቡብ 300 ኪሎ ሜትር በመግባት የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ተቆጣጠረ። የሶማሊያ ኃይል በተቆጣጠራቸው ቦታዎችም ንብረት ተዘረፈ፣ ሴቶች ተደፈሩ እንዲሁም በርካታ ሲቪል ዜጎች ወደ ሶማሊያ ከተሞች በገፍ ተጋዙ።

ሶማሊያ ወረራውን በጀመረችበት ወቅት በሁለቱ አገሮች የጦር ሠራዊቶች መካከል ከፍተኛ ልዩነት ነበር። ለአብነትም የሶማሊያ የምድር ጦር አወቃቀር 8 እግረኛ ክፍለ ጦር ሲኖራት፤ ኢትዮጵያ አራት ክፍለ ጦር ብቻ ነበራት። ኮማንዶ ብርጌድ እና ሜካናየዝድ ሶማሊያ 4 የነበራት ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ምንም አልነበራትም። ታንከኛ ብርጌድ እና መድፈኛ ብርጌድ ሶማሊያ 4 ሲኖራት ኢትዮጵያ አንድ ብቻ እንደነበራት ታሪክ ያሳያል።

በተጨማሪም ሶማሊያ የታጠቀችው የከባድ መሳሪያ ዓይነትና ብዛትም ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች 253፤ ኢትዮጵያ ደግሞ 51 ነበራት። ሶማሊያ 608 ታንኮች፣ ኢትዮጵያ 132 ታንኮች፤ ሶማሊያ 260 መድፎች፣ ኢትዮጵያ 48 መድፎች፤ ቢ.ኤም ሮኬቶች ሶማሊያ 125 ኢትዮጵያ አንድ፤ አየር መቃወሚያ ሚሳኤሎች ሶማሊያ 75 ኢትዮጵያ ደግሞ ምንም አልነበራትም።

በታጠቅ ጦር ሰፈር የነበረው ህዝባዊ ሠራዊትም በ9 ክፈለ ጦሮች ተዋቅሮ 8ኛ፣ 9ኛ፣ 10ኛ እና 11ና ክፍለ ጦሮች ወደ ምስራቅ፤ 12ተኛ ክፍለ ጦር ወደ ደቡብ፣ 14ና፣ 15ኛ፣ 16ኛ እና 17ኛ ክፈለ ጦሮችም ወደ ኤርትራና ትግራይ ተላኩ። የኩባ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮም አንጎላ ከነበረው ሠራዊታቸው 18 ሺህ ያህል የእግረኛ ተዋጊና የሜካናይዝድ ኃይል ከህክምና ባለሞያዎች ጋር በጀነራል ኦርላንዶ ኦችዋ አማካኝነት እየተመራ ወደ ኢትዮጵያ እንዲላክ አድርገዋል።

ይኼውም ህዝባዊ ሠራዊቱ ከመደበኛ ጦሩ ጋር በመቀላቀል በበርካታ ግንባሮች ተሰልፎ ነባሩን ጦር በማጠናከር የሶማሊያን ተጨማሪ መስፋፋት መግታት ጀመረ። እንዲሁም በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይልም በቁጥርና በዘመናዊነት የሚበልጡትን የሶማሊያ ሚጎች በአየር ላይ ውጊያ ከኢትዮጵያ የአየር ክልል ካጸዳ በኃላ የሶማሊያ ግዛት ላይ ዘልቆ በመግባት የነዳጅ ዴፖዎችን፣ የስንቅና ትጥቅ መጋዘኖችን እና ሌሎች ንብረቶችን ማውደም ጀመረ።

የአየር ኃይሉን ሽፋን እየተጠቀመ ህዝባዊ ሠራዊቱ ከህዳር አጋማሽ 1970 ጀምሮ ከመከላከል ደረጃ ወደ ሰፊ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ተሸጋገረ። በርካቶችም መስዋዕት እየሆኑ በሶማሊያ ኃይል ከበባ ውስጥ የነበሩትን ድሬዳዋ እና ሐረር ከተሞችን ማስጣል ቻለ። የካቲት 23 ቀን 1970 የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት በጭናቅሰን እና በቆሬ በኩል ወደ ጅጅጋ አቅጣጫ የተጠናከረ ቅንጅታዊ ማጥቅት ዘመቻ ከፈቶ ከሶማሊያ ጦር ጋር ተፋለመ።

ኾኖም ግን በሌላ አቅጣጫዎች ከጀልዴሳ ግንባር ሌላ ጥቃት ተከፈተበት። በዚህም ወቅት የሶማሊያ ጦር ከጅጅጋ በስተምዕራብ በኩል ባለው ካራማራ ተራራ ላይ ማዘዣ ጣቢያውን በመስራት በከፍተኛ ደረጃ ተከላከለ። በመጨረሻም እሁድ የካቲት 26 ቀን 1970 ረፋድ ከሞትና ከመቁሰል የተረፈው የሶማሊያ ሠራዊት ወደ ሀርጌሳ ሸሸ። በዚህም ኢትዮጵያ ሠራዊት ወድቆ የነበረውን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርጎ በክብር ሰቀለ።

በካራማራ ጦርነት በርካቶች ተሰውተዋል። በቀጣናው ያለውን ድርሻ ለማስፋት ኢትዮጵያን የወረረው ሜጀር ጄነራል ዚያድባሬ ከሽንፈቱ በኋላ ተቀባይነቱ እየሟሸሸ መጣ። በኋላም ‘ታላቋ’ የሚል ቅጥያ የነበራት ሶማሊያም ከኦጋዴን ጦርነት በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት መታመስ የጀመረች ሲሆን ዚያድባሬ በ1983 ከሥልጣን ወርደው ወደ ናይጄሪያ ሸሽተው ሕልፈተ ሕይወታቸውም ለአራት ዓመታት በቆየባት ናይጄሪያ ሆነ። 

ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ
ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ
ረጅሙን ጉዞ ጥንቱን አውቄ
ተነስቻለው ትጥቄን አጥብቄ
መብት ነፃነት እስኪሆን አቻ
ተነስቻለው ለድል ዘመቻ
ልሙት ልሰዋ ደስ ብሎኝ ስቄ
ለሀገሬ ክብር እኔ ወድቄ…
ሀገሬ መመኪያ ክብሬ
አትደፈርም ዳር ድንበሬ…
የካራማራ የድል ቀን የሚገባውን ያህል ያልተዘመረለት ትልቅ የታሪክ አካል እንደሆነ በርካቶች ያነሳሉ። ድሉ ከአድዋ ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን በዘር፣ በሀይማኖት እና በጎሳ ሳይከፋፈሉ ከሰሯቸው ተጠቃሽ የታሪክ አጋጣሚዎች አንዱ ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply