የኬንያውያኑ ተቃውሞ ቀጥሏል

የኬንያውያኑ ተቃውሞ ቀጥሏል

•  ተቃዋሚዎች “ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ይልቀቁ“ እያሉ ነው

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የኑሮ ውድነትን እንዲያሻቅብ ያደርገዋል የተባለውንና ላለፉት ሁለት ሳምንታት ለተቀሰቀሰው ህዝባዊ  ተቃውሞ ሰበብ የሆነውን የፋይናንስ ረቂቅ በፊርማዬ አላጸድቅም ብለው  ወደ ፓርላማ ቢመልሱትም፣ ተቃውሞው አሁንም  አልበረደም፡፡ በዛሬው ዕለት በናይሮቢና በሌሎች ከተሞች ለተቃውሞ የወጡ ኬንያውያን ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በመላ አገሪቱ በተቀጣጠለው ተቃውሞ ሳቢያ፣ ቢያንስ 39 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ የሰብአዊ መብት ተቋም አስታውቋል፡፡

በዛሬው ዕለት ማክሰኞ በናይሮቢና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን፤ ፖሊስ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ተቃውሞውን ለመበተን ሞክሯል – የተሳካለት ግን አይመስልም፡፡ ተቃዋሚዎችና ፖሊሶች ተፋጠው ነው የዋሉት ተብሏል፡፡

ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ሃሳባቸውን በመለወጥ በፋይናንስ ረቂቅ ህጉ ላይ ፊርማቸውን በማኖር ሊያጸድቁት ይችላሉ የሚል ስጋት በተቃዋሚዎች ዘንድ  ያረበበ ሲሆን፤ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ሩቶን በብልሹ አስተዳደር እየከሰሱና ከሥልጣን እንዲለቁ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከኬንያውያን ጋር ለመወያየት ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የተቃውሞው ንቅናቄ አባላቱ ግን የሩቶን የእንወያይ ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል፡፡

“ሰዎች በጎዳናዎች ላይ እየሞቱ ነው፤ እሱ (ሩቶ) የሚያወራው ግን ስለ ገንዘብ ብቻ ነው፡፡ እኛ ገንዘብ አይደለንም፡፡ እኛ ሰዎች ነን፡፡ እኛ የሰው ልጆች ነን፡፡” ሲል ለሮይተርስ የተናገረ አንድ የሞምባሳ ተቃዋሚ፤ “ፕሬዚዳንቱ ለህዝቦቹ ማሰብ አለበት፤ ምክንያቱም ለህዝቦቹ የማያስብ ከሆነ እኛም ወንበሩ ላይ እንዲቀመጥ አንፈልግም፡፡” ብሏል፡፡

የኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ መሰረት፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በመላ አገሪቱ በተቀጣጠለው ተቃውሞ ሳቢያ፣ ቢያንስ 39 ሰዎች በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ባለፈው እሁድ ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር ግን የሟቾች ቁጥር 19 መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የኬንያ ዋነኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ባለፉት ሳምንታት ለተከሰተው ሞት፣ የሩቶ መንግሥት ሃላፊነቱን እንዲወስድ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ ጠይቋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው ኬን ጊቺንጋ ለአሶሼትድ ፕሬስ በሰጡት ማብራሪያ፤ መንግሥት ኢኮኖሚው እንዲዳብር የሚያስችለውን የታክስ ማሻሻያ ለማድረግ የተለየ አቅጣጫ  መከተል አለበት፤ ብለዋል፡፡

በኬንያ ሥራ አጥነት በናጠጠበትና የኑሮ ውድነት በናረበት ሁኔታ፣ የፕሬዚዳንቱና ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው የተቀማጠለ ህይወት መምራት በህዝቡ ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱን  ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተቃውሞ የቀሰቀሰውን የፋይናንስ ረቂቅ ህግ በፊርማቸው ባለማጽደቅ የኬንያውያኑን ጥያቄ የመለሱ ቢሆንም፣ ተቃዋሚዎች ግን በእርሳቸው ላይ እምነት እንደሌላቸው እየገለጹ  ነው – በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የገቡትን ቃል ያላከበሩ “ውሸታም መሪ” ናቸው በሚል፡፡ ለዚህም ነው “ሩቶ ከሥልጣን ይልቀቁ” የሚለው ድምጽ የበረታው፡፡

በሌላ በኩል፣ የኬንያ የአሁኑ ተቃውሞ በማህበራዊ ሚዲያ የተደራጀና መሪ- አልባ በመሆኑ ምክንያት፣ መንግሥት እንደ ወትሮው ሊቆጣጠረውና ሊያፍነው አዳግቶታል ነው የሚባለው፡፡ የወጣት ኬንያውያኑ ጥያቄ አሁን አንድና አንድ ብቻ ሆኗል – ”ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ይልቀቁ“፡፡ የኬንያ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን ይለቁ ይሆን? የኬንያ ተቃውሞስ እንዴት ነው የሚበርደውና ኬንያውያን ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው የሚመለሱት? ለጊዜው ማንም መልስ ያለው አይመስልም፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply