(በአባቱ መረቀ)
አሜሪካ የክለስተር ቦምብን ለዩክሬን አስታጥቃለሁ ማለቷ ወዳጆቿን ጭምር አስቆጥቷል
ሩሲያ በበኩሏ ውሳኔው አደገኛ ውድመት የሚያስከትል የፈሪዎች ውሳኔ ስትል አስጠንቅቃለች፡፡
ሰዉ በላዉን እልቂት የእድሜ ዘመናቸዉንና የዲፕሎማሲ ልምዳቸዉን ተጠቅመዉ ሰላም ከማዉረድ ይልቅ ዘመኑ የወለዳቸዉን አዉዳሚ የጦር መሳሪያን ለዩክሬን በአፍ በአፏ እያጎረሱ የጦርነቱን ዕድሜ ማራዘምን አማራጭ አድርገዋል በሃያሏ አሜሪካ የሚመሩት የምእራቡ አለም ሀገራት፡፡
5 መቶ ሁለት ቀናት ሙሉ ሞት ዉድመት ስደትና መንከራተት ሆኗል የዩክሬናዉያን እጠፋንታ፡፡
የዩክሬንና የሩሲያ ወታደሮችም በቁሩም በነዲዱም ለእንቆቅልሹ እልቂት ይዋደቃሉ፡፡
የምዕባዉያን በእጅ አዙር በጦርነቱ መሳተፍ የሩሲያን ትእግስት እየተፈታተነ እንደሚገኝም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በተደጋጋሚ ቢያሳስቡም እነ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ግን አሁንም በጦርነቱ ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ነዉ ይላል የአልጄዚራ የታስና የቢቢሲ ዘገባ፡፡
ከሰሞኑ የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ድንገት የክላስተር ቦምብን ለዩክሬን እናስታጥቃለን በማለታቸዉ የዩክሬን አመራሮችን ጮቤ ቢያስረግጥም ሩሲያን ቢያስቆጣም የአሜሪካን ወዳጆች ግን ጭንቀት ዉስጥ ከቷል ነዉ የተባለዉ፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ፀኃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግም ይህን የለሁበትም ሲሉ ተናግረዉ ግን ደግሞ ለዩክሬን ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን እናቀርባለን ሲሉ አስታዉቀዋል፡፡
ስፔንን የመሳሰሉ ሀገራትም ከደሙ ንጹህ ነን የሚል ድምፅ እያሰሙ ነዉ፡፡
የመንግስታቱ ድርጅትም ይህ አደገኛ መዘዝ ይዞ የሚመጣ ነዉ ሲል አሜሪካን አሳስቧል፡፡
የአሜሪካን ውሳኔን አሳስቦናል ካሉ የዋሽንግተን አጋር አገራት መካከል ብሪታንያ ካናዳ፣ ኒው ዚላንድ ካምቦዲያ እና ስፔን ይገኙበታል።
ክላስተር ቦምቦች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ከ100 በላይ በሆኑ አገራት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እና እንዳይመረቱ ታግደዋል።
በክላስተር ቦምብ ውስጥ በርካታ ቦምቦች የታጨቁበት ሲሆን በሚፈንዳበት ጊዜ ወደ ብዙ ፍንጣሪ ቦምቦች በመለወጥ በፍንዳታው አካባቢ የሚያገኘውን ሰው በጅምላ ይሚገድል ነው።
ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ቦምቦች ተወርውረው ሳይፈነዱ የሚቀሩባቸው አጋጣሚዎች ከፍተኛ በሆኑ እንዲሁም ለረዥም ዓመታት መሬት ውስጥ ከቆዩ በኋላ ድንገት ስለሚፈነዱ አነጋጋሪ ናቸው።
ፕሬዝዳንት ባይደን ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ የ800 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ አካል የሆኑትን የክላስተር ቦምቦችን ለዩክሬን ስለመላክ ከአጋር አገራት ጋር መወያየታቸውን አስታዉቀዉ ነበር።
በዚህ ዉሳኔ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ቢደሰቱም በኔቶ አባል ሀገራት መካከል ልዩነትን ፈጥሯል፡፡
የኔቶ አባል ሀገራት ብቻም ሳይሆኑ ካምቦዲያን የመሳሰሉ ሀገራትም ዉሳኔዉ የሚበጅ ሳይሆን አለምን ለስጋት የሚዳርግ ነዉ እያሉ ነዉ፡፡
የካምፖዲያዉ ጠቅላይ ሚኒስትተር ሃን ሴን ዩክሬን እነዚህን የጦር መሳሪያዎች የምትጠቀም ከሆነ በራሷ ላይ ሞትን እንደመፍረድ ይቆጠራል ነዉ ያሉት ፡፡
“ለዚህ ደግሞ እኛ ካምቦዲያዎች ማሳያ ነን ምክንያቱም ያኔ በ1970ዎቹ አሜሪካ የክላስተር ቦምብ አዝንባብን ይሄዉ እስከዛሬ ጠባሳዉ አልሻረም” ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሃን ሴን፡፡
ይህ ድርጊት ከተፈፀመ ግማሽ ምእተ አመት ቢቆጠርም ዛሬም ቁስሉን ታሪክ ማከም አልቻለም ሲሉም የካለስተር ቦምቦችን አደገኝነት አስታዉቀዋል፡፡
በተጨማሪም የአሜሪካ የክላስተር ቦምቦችን ወደ ዩክሬን የመላክ ውሳኔ በተለያዩ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ዉግዘት ደርሶበታል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጦርነቱ ካበቃ በኋላ እንኳ ክለስተር ቦምቦች ለሰላማዊ ሰዎች ከፍተኛ ስጋት ናቸው ብሏል።
የዩክሬን አለቆች ግን ክላስተር ቦምቦችን መታጠቃቸዉን እንጅ ምን ሊያስከትልባቸዉ እንደሚችል መዘዙን የዘነጉት ይመስላል፡፡
የፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አማካሪዉ ሚኪያሂሎ ፖዶልያክ በቲዉተር ሰሌዳቸዉን ባሰፈሩት ፅሁፍ ክላስተር ቦምቦች የሩሲያን ጦር አደብ ለማስገዛት ሁነኛዉ መፍትሄ ናቸዉ ብለዋል፡፡
ሩሲያ ይሕንን መሳሪያ በእኛ ላይ ተጠቅማለች ስለዚህ ይህ ሊያስገርም አይገባም ያሉት አማካሪዉ በቀጣይ የመልሶ ማጥቀት ዘመቻዉን ያነቃቃሉ ብለዋል፡፡
ሞስኮ ግን የአሜሪካን ዉሳኔ አደገኛ መዘዝ ሊስከትል የሚችል የፈሪዎች ዉሳኔ ብለዋለች፡፡
ሞስኮ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለዩክሬን ክላስተር ቦምብን አስታጥቃለሁ ማለቱን ተከትሎ ፈሪ ሀገር ነች ስትል ወርፋታለች፡፡
የሩሲያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ በሰጡት መግለጫ የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የክላሰተር ቦምብ ለዩክሬን መለገሳቸዉ ፈሪና ደካማ መሀናቸዉን ያሳያል ሲሉ መናገራቸዉን አረቲና አልጄዚራ አስነብበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዉሳኔዉ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ በገፍ ሲያቀርቡ የነበሩ ሀገራት አሁንላይ ተስፋ እየቆረጡ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል ቃል አቀባይዋ ማሪያ ዛካሮቫ፡፡
የክላስተር ቦምብን ዩክሬን ታጠቀችም አልታጠቀችም ከመቀጥቀጥ ግን እንደማተርፍም አስምረዉበታል፡፡
በሌላ በኩል የክላስተር ቦምብን አስመልክቶ በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል ሀገራት መካከል ከፍተኛ ልዩነት መታየቱም እንደቀጠለ ነዉ፡፡
የስፔን መንግስትም በግልጽ ይህ የጦር መሳሪያ ለዩክሬን መሰጠጥ የለበትም ሲል ማሳሰቡን የአልጄዚራ ዘገባ ያሳያል፡፡
የስፔን የመከላከያ ሚኒስቴር በሰጠዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ ማንኛዉም የምእራቡ አለም ሀገራት ለዩክሬን የሚሰጡት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ዩክሬን እራሷን እንድትከላከል እንጅ ሩሲ ላይ ከባድ ዉድመት አድርሳ ሌላ መዘዝ እንዳትስከትል አይደለም ሲል አስጠንቅቋል፡፡
የክላስተር ቦምብን ላለመጠቀም ስምምነት ላይ ከደረሱ 1 ሀገራት መካከል ስፔን አንዷ ነች፡፡
የሰሜን አተለንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸኃፊ ጄንስ ስተልተንበርግም ሀገራት የክላስተር ቦምብን ሲፈልጉ ለዩክሬን ይስጡ ካልፈለጉም ይተዉት ብለዋል፡፡
የነጩ ቤተመንግስት ሰዎችም እሳቱን ከማጥፋት ማጋጋልን አማራጭ አድርገዋል እየተባለ ነዉ፡፡
ሐምሌ 03 ቀን 2015 ዓ.ም
Source: Link to the Post