የክልል መንግስታት ያቋቋሟቸው የልዩ ኃይሎች አባላት “ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ” የሚያደርግ “ተግባራዊ እንቅስቃሴ” መጀመሩን የፌደራል መንግስት አስታወቀ። የክልሎች የልዩ ኃይል አባላት እንደ ፍላጎታቸው ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም የክልል ፖሊስ አባልነት መካተት እንደሚችሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
በሁሉም ክልሎች አመራሮች ጥናት የተደረገበት የልዩ ኃይል አባላትን ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች የማስገባት ውሳኔ “ያለምንም ልዩነት” ስምምነት ላይ የተደረሰበት እንደሆነ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 28፤ 2015 ባወጣው መግለጫ አትቷል፡፡ እርምጃው “የኢኮኖሚ አቅማችንን በማሰባሰብ የሠራዊታችንን የሥልጠና፣ የትጥቅ እና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ አለው” ያለው የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቱ፤ ይህንኑ በመረዳትም “በሁሉም ክልሎች ሂደቱ በመግባባትና በውይይት እየተከናወነ” እንደሚገኝ ገልጿል።
ይሁንና በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ “ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት” መታየታቸውን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው አስታውቋል። በአማራ ክልል የተፈጠረው ኩነት “በአንድ በኩል የመልሶ ማደራጀት ስራውን እና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሀሰት ወሬ በመጠለፍ” የተከሰተ እንደሆነ በመግለጫው ጠቁሟል።
መንግስት በስም ባይጠቅሳቸውም “ሂደቱን ለማደናቀፍ” ይፈልጋሉ ያላቸው ኃይሎች “የመልሶ ማደራጀቱ መርኃ ግብር በአማራ ክልል ብቻ እየተካሄደ ነው፤ ህወሓት ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት የክልሉ ልዩ ኃይል ትጥቅ ይፈታል” የሚሉ “የሀሰት አጀንዳዎች” እያናፈሱ እንደሆነ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ይታከልበታል]
The post የክልል ልዩ ኃይሎች አባላት “ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ” የሚያደርግ “ተግባራዊ እንቅስቃሴ” መጀመሩን መንግስት ገለጸ appeared first on Ethiopia Insider.
Source: Link to the Post