የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ስርዓቱ በዲጂታል መደረጉን ተከትሎ አቅመ ደካሞች እና ለቴክኖሎጂው እንግዳ የሆኑ ሰዎች ለክፍያ ስርዓቱ እንግዳ በመሆናቸው እና ችሎታው ባለመኖሩ የአገልግሎት ክፍያውን በወቅቱ ለመክፈል መቸገራቸውን እያነሱ ነው፡፡
በዚህም ለቅጣት እና አገልግሎቱ እስከመቋረጥ ሊደርስብን ይችላል በሚል ስጋት ውስጥ ከቶናል ሲሉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ በዲጅታል እንዲሆን ሲደረግ፣ የተለያዩ ቀላል የመክፈያ አማራጮችን ይዞ የመጣ ቢሆንም፣ በህብረተሰበ ዘንድ ከፍተኛ የግንዛቤ ውስንነት አንዳለም በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡
የኢትዮጲያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዪ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ደግሞ
ለአጠቃቀም አስቸጋሪ ነው የሚለውን ተቃማቸው እንደማይቀበለው በማንሳት ‹‹የዲጂታል ክፍያ ስርዓቱን ከአንድ አመት በፊት ነው የተጀመረው ደምበኞችንም የማለማመድ ስራውን ስንሰራ ቆይተናል›› ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ከሃምሌ አንድ ጀምሮ በዚሁ ዘመናዊ ክፍያ አማራጮች የፍጆታ ክፍያውን ከዚሁ በፊት ይከፍሉበት በነበረው የጊዜ ሰሌዳ መክፈል ግዴታ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ‹‹ከአጠቃቀም ውስንነት ጋር ለተነሳው ደግሞ በየ አካባቢው ባሉ የቴሌብር ወኪሎች፣ የሲቢኢ ብር ወኪሎች በመኖራቸው እነርሱን እንዳማራጭ በመውሰድ መጠቀም ይቻላል ›› ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ተቋሙ ከዚህ በፊት ለክፍያ አገልግሎት ይሰጥባቸው የነበሩ ቅርንጫፍ መስርያ ቤቶች ዝግ እንዳልሆኑም በማንሳት ለመክፈል ተቸግረናል የሚሉ ደምበኞች በመሄድ ባሉት ሰራተኞች በዲጂታሉ እንዲከፍሉ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልፀዋል፡፡
በተቋሙ አሰራር መሰረት በወቅቱ ክፈያቸውን ያልፈፀሙ ደንበኞች የመክፈያ ጊዜያቸው ከተጠናቀቀበት ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 7 ቀናት በየቀኑ የሚሰላ ቅጣት እንዲከፍሉ የሚደረግ ሲሆን እንዲሁም በ13ኛው ቀን ኃይል የሚቋረጥ እንደሚሆን ተቀምጧል፡፡
በተጨማሪም የተቋረጠውን ኃይል መልሶ ለማገኛኘት ለነጠላ ፌዝ ቆጣሪ 500 ብር እንዲሁም ለሦስት ፌዝ ቆጣሪ 1000 ብር እንዲከፈል ይደረጋል፡፡
በረድኤት ገበየሁ
ሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም
Source: Link to the Post