የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች የትምህርት ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን በ2013 የተቀላቀሉ ተማሪዎች ከሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ጀምሮ የመመረቂያ ጊዜ ተራዝሞብናል በሚል ትምህርት የማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። 

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን የገለጹት ተማሪዎች የትምህርት ማቆም አድማውን ያደረጉት የትምህርት አሰጣጡ “ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አንጻር ወደኋላ የቀረ” በመሆኑ እንዲሁም በዚህ በ2016 መሆን የሚገባው የምርቃት ፕሮግራማቸው አንድ ዓመት ወደ ኋላ በመቅረቱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው “በተደጋጋሚ ወደ ኋላ የቀረንበትን ትምህርት ሸፍነን በዚህ ዓመት እንዲያስመርቀን ጠይቀናል” የሚሉት ተማሪዎቹ “አንድም ችግራችንን ለመፍታት የሚሞክር አካል በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የለም” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።

ቤተሰቦቻቸው በዚህ ዓመት እንደሚመረቁ እንደሚያውቁ የሚገልጹት ተማሪዎች፤ ወደዩኒቨርሲቲው ከሩቅ ቦታ የሚመጡ ተማሪዎች ላይ አንድ ዓመት ሲጨመር ቤተሰብን ተጨማሪ ወጪ ማስቸገር ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም እኩል ወደዩኒቨርሲቲ ከገቡ አቻዎቻቸው ወደኋላ መቅረቱ በራሱ “ሌላ ጫና ይፈጥርብናል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። 

“መቼ ተምረን ጨርሰን፣ መቼ የመውጫ ፈተና ተፈትነን መቼ እንደምንመረቅ አናውቅም” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢ ተማሪዎቹ፤ “ጥያቄያችንን ለማን አቅርበን ማን እንደሚፈታልን ግራ ተጋብተናል” ይላሉ። ይሁን እንጂ ጥያቄያቸውን በሠላማዊ ሰልፍ ለማቅርብ መሞከራቸውን ገልጸው “ለፌደራሎች እና ለጥበቃዎች እርምጃ እንዲወሰድብን ትዕዛዝ ተሰጥቷል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ወደ መማሪያ ክፍል ካልገባችሁ “በፌደራል ፖሊስ ከዶርም እየወጣቹ እንድትገቡ ይደረጋል” መባላቸውን ተማሪዎቹ ጨምረው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደተማሪዎቹ ቅሬታ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ውሳኔ የተነሳ “ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ወደ ሱስ እንዲሁም ተስፋ የቆረጡ ተማሪዎች ደግሞ ግቢውን ለቀው እየወጡ” ይገኛሉ።

አዲስ ማለዳ ከጥቅምት 16 ቀን 2016 ጀምሮ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው በትምህርት ሚኒስቴር የተሾሙትን ጉቼ ጉሌ (ዶ/ር) ለማናገር ወደ ዩኒቨርሲቲው የቢሮ ስልክ የደወለች ቢሆንም የቢሮውን ስልክ ምላሽ የሰጡት ሴት የአዲስ ማለዳን ጥያቄ ከሰሙ በኋላ ስልኩን በመዝጋታቸውን በድጋሚ ስልክ ባለመመለሳቸው ሳይሳካ ቀርቷል። 

በ2013 ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀሉ ተማሪዎች በአሁኑ ሰዓት የአራተኛ ዓመት ሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ላይ የደረሱ ቢሆንም የወላይታ ሶዶ ተመራቂ ተማሪዎች ግን “ሶስተኛ ዓመት ሁለተኛ መንፈቅ ዓመት” ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ተማሪዎቹ አክለውም “የሶስተኛ ዓመት የሁለተኛ መንፈቀ ዓመት ምዝገባ ለማድረግ የምናቀርበው የሶስተኛ ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ ውጤት (Grade report) ላይ 4ኛ ዓመት እንደሆንን ነው የሚያሳየው” ብለዋል። 

ይኼው አካሄድ ያልገባቸው ተመራቂ ተማሪዎችም ምናልባትም “ዩኒቨርሲቲው ክፍተቱን ከትምህርት ሚኒስቴር ለመሸፈን  ያደረገው” ሊሆን እንደሚልችል ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል። 

ሆኖም “ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ማስረጃዎችን የመንግሥት የሥራ መፈለጊያ ጊዜ ገደብ ሁለት ዓመት መሆኑን አሳውቋል” የሚሉት ተማሪዎቹ “እኛ ግን አንደኛውን ዓመት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ነን፤ ይህ እንዴት ይሆናል?”በማለት ይጠይቃሉ።
ትላንት ጥር 23 ቀን 2016 በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተማሪ ተወካይ የሆኑ “ጥቂት” ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጉቼ ጉሌ ጋር መገናኘታቸውን አዲስ ማለዳ የሰማች ሲሆን ፕሬዝዳንቱ “እርሳቸው ባልነበሩበት ወቅት የተፈጠረውን ስህተት ማስተካከል እንደማይችሉ” እንደነገሯቸው ታውቋል። በተጨማሪም በዚህ ዓመት መመረቅ  እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል።

አዲስ ማለዳ በዚሁ ጉዳይ ላይ የዩኒቨርሲቲውን የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ያናገረች ሲሆን “ተማሪዎች ያልተጣራ መረጃ ወስደው ነው። እኛም ያንን የተሳሳተ መረጃ ሰምተን የተቀየረ ነገር እንደሌለ አሳውቀናል” ብሏል። ማክሰኞ ዕለት ተማሪዎቹን ሰብስበው ማናገራቸውን የገለጸው የተማሪዎች ህብረት ዛሬ ዓርብ ጥር 24 ቀን 2016 “አነጋግረናቸው ዛሬ ሁሉም ተማሪ ክፍል ገብቷል። አንዳንድ ተማሪዎች ያልገቡም አሉ” ሲል ገልጿል።

በዚህ ዓመት መመረቅ አለብን የሚሉት ተማሪዎች መቼ ይመረቃሉ በሚል ለቀረበለት ጥያቄም “ሶስት መንፈቅ ዓመት ትምህርት ይቀራቸዋል። ይኼም የሚያስፈልገው ጊዜ ይታወቃል” በማለት በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል። በአንጻሩ ተማሪዎቹ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት የሆነው ተማሪ “ሊመረቅና ሊወጣ ስለሆነ” ለችግሩ መፍትሔ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በተማሪዎቹ ለተነሳው “የሶስተኛ ዓመት የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ትምህርት ለመጀምር ባለንበት የዉጤት ወረቀት በአራተኛ ዓመት ተመዝግቦ ነው ያለው” ማለታቸውን በተመለከተ “ውሸት ነው” የሚለው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንቱ፤ “መርሐ ግብሩ ሲዘጋጅ ተማሪው ከገባበት ቀን አንስቶ እስከሚያልቅ ድረስ በትክክል ይሄዳል እንጂ” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።  

የህብረቱ ፕሬዝዳንት ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲውን ትክክለኛ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ብቻ በመከታተል ሀሰተኛ ከሆኑ መረጃዎች ሊጠበቁ ይገባል ቢሉም ተማሪዎቹ አሁንም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ በዚህ ዘገባ ላይ የሚኖሩ ተጨማሪ መረጃዎችን ተከታትላ ታቀርባለች።  

Source: Link to the Post

Leave a Reply