“የወልቃይትና ራያ ማንነት የክልሉ መንግሥት የማይቀየር አቋም ነው”:- ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ሐሙስ ሐምሌ 14 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የወልቃይትና ራያ ማንነት የክልሉ መንግሥት የማይቀየር አቋም ነው ራያና ወልቃይት ሕዝቡም አማራ መሬቱም የአማራ ነው እነዚህን ቦታዎች ለማንም አሳልፈን አንሰጥም ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ርዕሰ መሥተዳድሩ ከደሴ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ የንጹሃን አማራዎች በወለጋና ሌሎች አካባቢዎች እየደረሰባቸው ያለው የግፍ ጭፍጨፋን የክልሉ መንግሥት እንዴት ሊያስቆም አስቧል የሚሉና የወልቃይትና ራያ ማንነት ጉዳይን በተመለከተ ከነዋሪዎች ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከነዋሪዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ የአማራን ሞት ለማስቀረት በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ችግሩን መቅረፍ የሚችሉ አካላት ጋር መሥራትና የሕዝባችንን ህመም ሰምተን ያለብንን ድርብ ሀላፊነት ለመወጣት ቀን ከሌት እንሠራለን ብለዋል።

ሕዝቡን የሚያስቆጨው የወገኖች መጨፍጨፋ የክልሉን መንግሥትም ይሰማዋል፤ ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሄ የምናመጣው ከሕዝባችን ጋር በጥምረት ስንሠራ ስለሆነ ከገባንበት ፈተና በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ። “የአማራ ሕዝብ ሞት ቢያመንም መፍትሄው ጊዜያዊ ጩኸት ባለመሆኑ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከሕዝባችን ጋር እንሠራለን” ሲሉም ገልጸዋል፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሠሩ ያሉ ኃይሎች በአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ማድረግ ስላለባቸው ንጹሃን አማራዎች በተለያዩ አካባቢዎች በግፍ እየተጨፈጨፉ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይህን የጠላት ዓላማ ለማክሸፍም በከፍተኛ ትኩረት እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የወገኖቻችን ሞት አያመንም ማለት እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባል ብለዋል ዶክተር ይልቃል።

ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለመታደግም የገጠመንን ፈተና በዘላቂነት ለመሻገር ከፌዴራል መንግሥት ጎን እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።

የወልቃይትና ራያ ማንነት የክልሉ መንግሥት የማይቀየር አቋም ነው ያሉት ርዕሰ መሥተዳድሩ ራያና ወልቃይት ሕዝቡም አማራ መሬቱም የአማራ ነው እነዚህን ቦታዎች ለማንም አሳልፈን አንሰጥም ሲሉም መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።

የአማራ ሕዝብና የክልሉ መንግሥት ሰላም ፈላጊ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ ሰላም ፈላጊዎች ብንሆንም የጠላትን ወረራ ለመመከት ግን ሁሌም ዝግጁ ነን። የጠላትን ወረራ መመከት የሚያስችል አስተማማኝ ቁመና ላይም እንገኛለን ብለዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply